የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ለአስመራ እግር ኳስ ፌድሬሽን የወዳጅነት ጨዋታ ጥያቄ አቀረበ

1685

ጎንደር ሰኔ 4/2010 በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል የተጀመረውን አዲስ ግንኙነት ለማጠናከር የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የወዳጅነት ጨዋታ ለማካሄድ መዘጋጀቱን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አስታወቁ፡፡

ከንቲባው አቶ ተቀባ ተባባል ለኢዜአ እንደተናገሩት ሁለቱ አገራት በስፖርቱ መስክ የነበራቸውን የቆየ ወዳጅነት ለማጠናከር እንዲቻል አስተዳደሩ ለአስመራ እግር ኳስ ፌደሬሽን የወዳጅነት ጨዋታ ለማካሄድ በደብዳቤ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

“የኢትዮ-ኤርትራን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የሰላም፣ የፍቅርና የመደመር መርህ አጉልቶ ለማውጣት የስፖርት ከለቡ በስፖርቱ መስክ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ከኤርትራ ጋር ዘመናት የተሻገሩ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር የነበረውና በታሪክም ወደ አስመራ ለሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች የደረቅ ወደብ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር ከንቲባው አስታውሰዋል፡፡

ኤርትራውያን ከጎንደር ከተማ ህዝብ ጋር በባህልና በጋብቻ የተሳሰረ ታሪክ እንደነበራቸው አስታውሰው በስፖርቱ መስክም ቀደም ሲል የነበረውን ግኝኙነት ለማደስ በከተማ አስተዳደሩ በኩል ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልልን ወክሎ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው የፋሲል ከነማ የስፖርት ክለብ አስመራ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ለማካሄድ እንዲችል በመወሰኑ ለአስመራ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጥያቄ አቀርቦ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡