‘ማንም’ የተሰኘ አገር አቀፍ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ በይፋ ተጀመረ

115

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2012(ኢዜአ) ‘ማንም’ የተሰኘ አገር አቀፍ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ በይፋ ተጀምሯል።

በዘመቻው በነሃሴ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት 200 ሺህ ሰዎችን የመመርመር ዕቅድ ተይዟል።

የብሔራዊ የኮሮና ቫይረስ መከላከል የሚኒስትሮች ኮሚቴ የቫይረሱን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

ኮሚቴውን የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዘመቻው ከነገ ጀምሮ በይፋ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የቫይረሱን አገራዊ ስርጭት፤ የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ደግሞ ትምህርት ለማስጀመር መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች የተመለከቱ ጽሁፎችን አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ በርካታ ሰዎችን ከመረመሩ አገራት ተርታ እንደምትሰለፍ ገልጸው፤ ‘የምርመራ አቅማችን ካለን የሕዝብ ቁጥር አንጻር ሲመዘን እጅግ አናሳ ነው” ብለዋል።

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ሁከት የቫይረሱ ስርጭት እጅግ በመጨመሩ ‘ለመከላከሉ ስራ ይበልጥ ትኩረት እንድንሰጥ አስገድዶናል’ ነው ያሉት።

ከዚህ አንጻር ‘ማንም’ የተሰኘ አገር አቀፍ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በዘመቻው መሰረት በነሃሴ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት 200 ሺህ ሰዎችን ለመመርመርና በቤት ለቤት ልየታ ደግሞ 17 ሚሊዮን ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።

መንግስት ለዘመቻው አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም ነው የተናገሩት።

በዘመቻው የሚገኘው ውጤት በቀጣዩ ዓመት ለሚከናወኑ ተግባራት አመላካች መነሻዎችን እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር በተለይ ተማሪዎችና መምህራን በዘመቻው በመሳተፍ ረገድ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱም አሳስበዋል።

የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የማኅበረሰብ መሪዎች ለዘመቻው መሳካት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው ዘመቻው ዜጎችን ከመታደግ ባለፈ መንግስት ለሚወስዳቸው ቀጣይ እርምጃዎች ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

ኅብረተሰቡ ከራሱ ባለፈ የወገኖቹን ሕይወት ለመታደግ አስፈላጊውን ትብብርና ጥንቃቄ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች መካካል 92 በመቶ የሚሆኑት የቫይረሱ ምልክት እንዳልታየባቸው ከጤና ሚኒስትር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

እስካሁን ባለው ሂደት በቀን ያለው የመመርመር አቅም 11 ሺህ 450 ሲሆን በቅርቡ ሶስት ተጨማሪ ላቦራቶሪዎችን ወደ ስራ በማስገባት ቁጥሩ ወደ 15 ሺህ ከፍ እንደሚልም ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።