የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሳሪያ ማእቀብ ሊጥል ነው

71
አዲስ አበባ ሐምሌ 4/2010 የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በዚህ ሳምንት በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሳሪያ ማእቀብ ለመጣል ድምፅ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ማእቀቡ አንዲጣል የሚጠይቀው ምክረ - ሀሳብ የቀረበው የደቡብ ሱዳን ዋነኛ እርዳታ አቅራቢ በሆነችው እና በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2011 ነጻነቷን አንድታገኝም ከፍተኛ ድጋፍ ስታደርግ በነበረችው የአሜሪካ መንግስት ነው። አሜሪካ ለፀጥታው ምክር ቤት ባቀረበችው ረቂቅ ምክረ-ሀሳብ ላይ እንደተመለከተው በደቡብ ሱዳን ጥላቻን ለማስወገድና የሚፈፀሙ ሞራል የጎደላቸው ተግባራትን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት በሀገሪቱ ተፋላሚ ወገኖች መሪዎች ዘንድ ፍቃደኝነት የለም። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መምጣቱን አብራርቷል። ረቂቅ ምክረ-ሀሳቡ እስከ መጪው የፈረንጆቹ ግንቦት ወር 2019 ድረስ የሚዘልቅ የጦር መሳሪያ ማእቀብ በደቡብ ሱዳን ላይ እንዲጣል ይጠይቃል። ማንኛውም የመንግስታቱ ድርጅት አባል ሀገር ወደ ደቡብ ሱዳን የሚያመሩ የጦር መሳሪያ ጭነቶችን የማስወገድ ስልጣን ይሰጠዋል። አዲሱ ማእቀብ ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ላይ ተጥለው የነበሩ ማእቀቦችንም የሚያጠናክር ነው ተብሏል። የፀጥታው ምክር ቤት አባል የሆኑት ሩሲያና ቻይና ማእቀቡ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አማካኝነት እየተካሄደ ያለውና በአሁኑ ወቅት አዎንታዊ ለውጥ ያመጣው የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድርን ያደናቅፋል የሚል ስጋት አላቸው። በዚህም ምክንያት ከዚሀ በፊት በሀገሪቱ ላይ የተጣለው ማእቀብ የበለጠ እንዲጠናከር ፍላጎት የላቸውም ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በኢጋድ አማካኝነት በተደረገው የሰላም ጥረት ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና ተቀናቃኛቸው ሬክ ማቻር በሀገሪቱ ያለውን የፀጥታ ችግር ይፈታል የተባለ ስምምነት ባለፈው ሳምንት በካርቱም ፈርመዋል። ስምምነቱ ሁለቱ ወገኖች ዜጎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ያሰፈሯቸውን ወታደሮች ማንሳት፣ ወታደሮቻቸውን በመቀላቀል በአንድ እዝ ውስጥ ለማሰባሰብ ቀነ-ገደብ ማስቀመጥንና የጦር ሰራዊቱ የሚሰፈርበትን ቦታ መወሰንን የሚያካትት ነው። የስምምነቱን ተግባራዊነት የሚከታተል አንድ የጋራ የፀጥታ ኮሚቴ ለማቋቋምም ሁለቱ ወገኖች የተስማሙ ቢሆንም አሜሪካና የአውሮፓ ተባባሪዎቿ ሰሞኑን በተፈረሙት ስምምነቶች ትግበራ ላይ ጥርጣሬ አላቸው። በመሆኑም የሰላም ሂደቱን በአግባቡ ወደፊት መግፋት ይቻል ዘንድ በተፋላሚዎቹ ላይ የሚቻለው ሁሉ ከፍተኛ ተፅእኖ ሊደረግ ይገባል የሚል አምነትን ያራምዳሉ። በደቡብ ሱዳን አራት ዓመት ከመንፈቅ ያስቆጠረው የእርስ በርስ ግጭት ከ50 ሺህ በላይ ዜጎችን ህይወት የቀጠፈ ከመሆኑም በላይ አራት ሚሊዮን ዜጎችን አፈናቅሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም