የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት ታሪካዊ መሆኑን ገለፀ

58
ሐምሌ 4/2010 በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያና ኤርትራ ለ20 ዓመታት የቆየውን በጠላትነት የመተያየት ሂደት ቋጭተው የሰላም ስምምነት መፈረማቸው ታሪካዊ መሆኑን ገለፀ። ስምምነቱ ለምስራቅ አፍሪካና ለሌላው ዓለም የሚያበረክተው አስተዋጽኦም የጎላ መሆኑን ነው ያስታወቀው፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳኢያስ አፈወርቂ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማደስ እና  አዲስ የወዳጅነትና የትብብር ግንኙነት ለመጀመር ስምምነት በመፈራረማቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባም ገልጿል። ሁለቱ ሀገራት የተስማሙበት የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመስማማታቸው የፀጥታው ምክር ቤት አድናቆቱን ገልጿል። ምክር ቤቱ ስምምነቱ እንዲተገበር  ሁለቱን ሀገራት እንደሚያግዝም አረጋግጧል። ኢትዮጵያና ኤርትራ ለ20 ዓመታት በመካከላቸው የቆየውን ጦርነት፣ አለመግባባትና ፍጥጫ ቋጭተው አዲስ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት ተፈራርመዋል። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ፣ አየር መንገዶችን ስራ ለማስጀመር፣ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ በባህል እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አብረው ለመስራት ተስማምተዋል። ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የስልክ ግንኙነትም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣዩ ሳምንት በቦይንግ 787 አውሮፕላን በረራ እንደሚጀምርም ተነግሯል። ምንጭ፦www.washingtonpost.com
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም