አመልድ ኮሮናን ለመከላከል ከ4 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

60

ደብረ ብርሃን ሃምሌ 25/2012 የአማራ መልሶ ማቋቋም ልማት ድርጅት/አመልድ/ በሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙ ሶስት ወረዳዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚውል ከ4 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። 

በድርጅቱ የዋሽና መስኖ ፕሮግራም ማኔጀር አቶ አፈወርቅ ተክለማሪያም በርክክቡ ላይ እንደገለጹት አስቸጋሪውን የኮሮና ወቅት ለማለፍ መደጋገፍና መረዳዳት የዜግነት ግዴታ ነው ብለዋል ።

በዚህም ድርጅታቸው 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ፣ ሳኒታይዘር ፣ አልኮል፣ የእጅ መታጠቢያ ሳሙናዎችንና  የእጅ ጓንቶችን ድጋፍ አድርጓል።

የውኃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች 81 ሮቶ የተባለውን የውሃ ማጠራቀሚያ ጋንና የውሀ መቅጃ ጀሪካኖች ማበርከቱን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ያሉትን ባለሙያዎች በመጠቀምም የተበላሹ የውሃ ተቋማትን በመጠገን ህብረተሰቡ ንጽህናውን በመጠበቅ በሽታውን እንዲከላከል እየሰራ ነው ብለዋል።

 ድጋፉ የተደረገው በባሶና ወረና፣ በአንጎለላ፣ጠራና በሲያደብርና ዋዩ ወረዳዎች ለሚኖረው ህዝብ ነው ተብሏል ። 

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እንደ ሀገር  ከመንግስትና  ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን መመሪያዎች አክብሮ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑንም አቶ አፈወርቅ አሳስበዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል  አቶ ጥበቡ አበራ በበኩላቸው አመልድ ያደረገው ድጋፍ ወረርሽኙን ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

አሁን ላይ የሚስተዋለውን መዘናጋት በማስወገድ ቁርጠኛ የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ የቁሳቁስ ድጋፍ እጥረት እንደ አንድ ችግር እየተነሳ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

በዚህም ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ባለሃብቶች የአመልድን ፈለግ በመከተል ተከታታይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሲያደብርና ዋዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ሰይፉ በሰጡት አስተያየት የተደረገው ድጋፍ አርሶ አደሩ ጤናው ተጠብቆ የግብርና ስራውን በአግባቡ እንዲያከናውን የሚያግዝ ነው ።

የባሶና ወራና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታጠቅ ገድለአማኑኤል በበኩላቸው አመልድ በወረዳው ንፁህ የመጠጥ ውኃ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች የሚያከናውናቸው ተግባራት ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል ።

ድርጅቱ ያደረገውን ድጋፍ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ በመስጠት እንደሚሰራጭ የስራ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም