የፈረንሣይ ከፍተኛ የሽልማት ማኅበር ለሕዝባዊ ሠራዊት ትምህርት ቤት ማዕድ አጋራ

59

ሐምሌ 25 2012 ዓ.ም (ኢዜአ) የፈረንሣይ ከፍተኛ የሽልማት ማኅበር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ለተቸገሩ የሕዝባዊ ሠራዊት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወላጆች ማዕድ አጋርተዋል። 

ማኅበሩ የማዕድ ማጋራት ድጋፉን ያደረገው ለ100 ተማሪዎች ወላጆች ነው።

በሶስት ዙር በተደረገው ድጋፍ የስንዴ ዱቄት፣ ጤፍ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ሩዝ፣ የምግብ ዘይት እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ ሳሙናዎች ተበርክተዋል፤ ቁሳቁሱ በገንዘብ ሲሰላ 480 ሺህ ብር ግምት አለው።

የፈረንሳይ ከፍተኛ የሽልማት ማኅበር ፕሬዚዳንት ወይዘሪት ትዕግስት ይልማ ማኅበሩ የተለያዩ የድጋፍ ስራዎችን እንደሚሰራና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ ለትምህርት ቤቱ ለ3ኛ ጊዜ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ማኅበሩ ለትምህርት ቤቱ የሚያደርገው ድጋፍ ተማሪዎቹ የኮሪያ ዘማቾች የልጅ ልጆች በመሆናቸው እንደሆነም አክለዋል።

ዘመቻው የኢትዮጵያና የፈረንሣይ ዘማቾች ተደጋግፈው ያለፉት ጊዜ በመሆኑ የዘማቾቹን የልጅ ልጆችና ወላጆች መደገፍ የሚያሻ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና የፈረንሣይን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ማኅበሩ እየሰራም ነው ብለዋል።

የሕዝባዊ ሠራዊት አፀደ ሕጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አብርሃም አጥናፉ የማኅበሩ ድጋፍ ለሌሎች አርዓያ መሆን ያለበት ነው ብለዋል።

በትምህርት ቤቱ ቀደም ሲልም የኑሮ ጫና ያለባቸውና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች እንደሚገኙ አንስተዋል።

በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ትምህርት ቤት በመዘጋቱ የምገባ ፕሮግራም የተቋረጠባቸው ተማሪዎች ጎዳና ወጥተው ምግብ ለማግኘት ራሳቸውን ለበሽታው በሚያጋልጥ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩም ገልጸዋል።

ማኅበሩ ባደረገው ተከታታይ ድጋፍ ግን ተማሪዎቹ ለተከታታይ ሁለት ወራት ምግብ ማግኘት ችለዋል።

በትምህርት ቤቱ 569 የአፀደ ሕጻናትና 2 ሺህ 127 የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 369 ተማሪዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና ድጋፍ የሚያሻቸው እንደሆኑ ተለይተዋል።

የዛሬው ድጋፍ ከእነዚህ መካከል ለ100ዎቹ ነው የተደረገው።

በድጋፉ ዘመን ባንክ፣ የሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ተማሪዎችና ቶታል ኢትዮጵያ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም