የበረሃ አንበጣ ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው– የግብርና ሚኒስቴር

224

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 24/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገባቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። 

የምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል ድርጅት በበኩሉ በምስራቅ አፍሪካ ክፍለ አህጉር ከሰኔ 2011ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል የተካሄዱ ተግባራት ስጋቱን ቀንሰውታል ብሏል።

የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት በቅርቡ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በአንድ አጻፋ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንጋ 40 ሚሊዮን የሚሆን አንበጣ የሚይዝ ሲሆን፤ በአንድ ቀን ብቻ 35 ሺህ ሰዎች ሊመገቡት የሚችሉትን አዝርዕት ያጠፋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ታምሩ ከበደ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ባለፈው አንድ ዓመት መንጋውን በመከላከል ሒደት የተገኙት ልምዶች ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን አግዟል።

በሶማሌ ክልል የተፈለፈለው መንጋ በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ  ዞኖች በሰብል ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በተወሰዱ እርምጃዎች  3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መዳኑን  አቶ ታምሩ ተናግረዋል።

መንጋው ከተከሰተባቸው ሁሉም አካባቢዎች መረጃ በወቅቱ ስለሚመጣና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የመከላከል ሥራው ስለሚከናወን መንጋው የሚያስከትለው ጉዳት ላይ የነበረው ስጋት መቀነሱን አመልክተዋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በደቡብ ኢትዮጵያ የኬንያ ድንበርን ጨምሮ በቦረና ፣ጉጂ ዞኖችና በሁሉም የሶማሌ ክልል ወረዳዎችና ዞኖች ተራብቶ የነበረው መንጋ ስርጭት መቀነሱን ጠቁመዋል።

ለዚህም መንጋውን ለመከላከል የኅብረተሰብ ንቅናቄን በመፍጠር የአርብቶና የአርሶ አደሩ ግንዛቤ ማደጉ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተወካዩ አስታውቀዋል።

መንጋው በተለይ በአፋር ክልል ስምንት ወረዳዎች በከፍተኛ መጠን ተፈልፍሎ ሊያደርስ የነበረውን ጉዳት በተጠናከረ መልኩ መከላከል ተችሏል ብለዋል።

ነገር ግን በወረዳዎቹ ከቦታ አቀማመጥ አንፃር ሊደረስባቸው ባልቻሉ አካባቢዎች አንበጣው በመፈልፈል በምስራቅ አማራ፣በአፋር፣በደቡባዊ ትግራይ አዋሳኝ ቦታዎች በማሽላ ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

በመሆኑም እስካሁን መንጋውን ለመከላከል የተከናወኑት ተግባራት መንጋውን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ይሆናል ተብሎ አይገመትም ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት የአንበጣ መረጃና አሰባሰብ ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፈለገ ኤልያስ  በበኩላቸው በክፍለ አህጉሩ ጉዳት ሲያደርስ የቆየው መንጋ በአሁኑ ወቅት የንፋስ አቅጣጫ ተከትሎ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ እየሔደ በመሆኑ የስርጭቱን  ስጋት እንደሚቀንሰው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ መንጋውን ለመከላከል መረጃ በማቀበልና በመቀበል እየሔደችበት ያለው ርቀት ስርጭቱን ለመቀነስ እንዳስቻላትም ጠቁመዋል።