ሕወሃት ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ምስቅልቅል ምክንያት ነው

102

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 23/2012 (ኢዜአ) ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ለኢትዮጵያ አሁናዊ የፖለቲካ ምስቅልቅል ምክንያት እንደሆነ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች ገለፁ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የትግራይ ዴክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አመራሮች ''በትግራይ ክልል ያለው የዴሞክራሲ ምህዳር ተዘግቶ ከሕወሓት ውጭ አማራጭ ሃሳብ ማቅረብ ወንጀል ተደርጓል'' ይላሉ።

የትዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ መስፍን ደሳለኝ ክልሉ የሕወሃት ተቃዋሚዎች በባንዳነት የሚፈረጁበት፣ የሚሳደዱበትና የሚታሰሩበት እንደሆነ ገልጸዋል።

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ሃይሉ ክልሉ መንግስትና ፓርቲ ያልተለየበት፣ አማራጭ ሃሳብ ማንሳት የማይቻልበት ፖለቲካ ሁኔታ ተባብሶ የመቀጠሉን ሃሳብ ይጋራሉ።

የሕወሃትን አስተሳስብ የሚቃወሙ የትዴፓ አባላት ተለይተው እየተሳደዱና እየታሰሩ እንደሆነ አንስተዋል።

በሃሳብ የበላይነት የማያምነውና ለሁሉም ነገር ብቸኛ አድራጊ፣ ፈጣሪ አድርጎ ራሱን የሚያየው ሕወሃት ለትግራይ ህዝብ 'ትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ደርግ ሆኗል' ይላሉ።

ሕወሃት የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ በማራመድ፣ ህዝብን እርስ በርስ በማጋጨት በሴራ ፖለቲካ ሲሰራ እንደነበር አመራሮቹ ይገልጻሉ።

ፌዴራሊዝም አወቃቀርና አተገባበርም ለውስን ባለስልጣናት ብቻ የሚመች፣ በውሸት ትርክት ሰውን ከሰው ከማንነቱ ይልቅ ቋንቋን የመለያያ መሳሪያ በማድረግ ይጠቀምበት እንደነበር ገልጸዋል።

የነበረው አሰራር የፌዴራሊዝም ሳይሆን የተማከለ ስልጣን የበዛበት አሃዳዊ እንደነበር ገልጸው፤ በዚህም ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁናዊ ምስቅልቅል ተጠያቂ ሕወሃት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከለውጡ በኋላም "ሕወሃት የሚቃወመው አሃዳዊነትን ሳይሆን አገራዊ አንድነትን ነው" ብለዋል።

ሕወሓት ወደስልጣን ከመምጣቱ በፊት የትግራይ ህዝብ በየትኛውም የአገሪቱ አካበቢ ህዝብ እንደነበር አስታውሰው፤ ሕወሃት በትግራይ ህዝብ ስም በመነገዱ ምክንያት ለችግር መዳረጉን አንስተዋል።

በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግደው የህወሃት ቡድን ተጠያቂነት ሲመጣበት ትግራይ በመሆኑ እንደሆነ የሚገልጽ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሕወሃትና የትግራይን ህዝብ የተለያዩ መሆናቸውን እንዲገነዘብና ለሕወሃት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሌለበት ጥሪ አቅርበዋል።

የሕወሃት አመራሮች አገር ሰላም ከሆነ የተጠያቂነት ስጋት እንዳለባቸው የሚገልጹት የትዴፓ አመራሮች፤ በምርጫና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚያነሱት ተቃርኖም ከዚህ የሚመነጭ እንደሆነ ይናገራሉ።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሕልውና ችግር በሆነበት አጋጣሚ በአንድ በኩል ጦርነት እያወጀና ሰውን እያሳደደ በሌላ በኩል 'ምርጫ አደርጋለሁ' ማለቱ በጦርነት ውስጥ ሰርግ የመደገስ ያህል እብደት እንደሆነ ገልጸዋል።

'ግድቡ ተሽጧል' የሚሉ የሕወሃት አመራሮች ለርካሽ ፖለቲካ ትርፍ እንደሆነ ገልጸው፤ የሙስና ወንጀል በመፈጸም የግድቡ ግንባታ እንዲቆም ያደረጉበት ወቅት እንደነበር አስታውሰዋል።

የሕወሃት ሰዎች በቀድሞ ስልጣናቸው ኢትዮጵያን ያለባሕር በር እንድትቀር ያደረጉ መሆናቸውን በመጥቀስም፤ ህወሃት ለግል ጥቅም እንጂ ለአገር ጥቅምና ሉዓላዊነት ዘብ ቆሞ እንደማያውቅ ተናግረዋል።

አብሮ የመስራት ባህሪ የሌለው ሕወሃት የአስተሳሰብ ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል ይገልጻሉ።

የፌዴራል መንግስቱ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 62 መሰረት ሕግ ሲጣስ መጠየቅ ወይም የፌዴራል መንግስቱ ሃላፊነቱን ባለመወጣት ራሱን የሚያስጠይቀው እንደሆነ ተናግረዋል።

በህዝብ ስም እየነገዱ ትግራይ የመሸጉ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል።

የትግራይ ህዝብ በተለየም ወጣቱ ለሰላም፣ ለልማት፣ ለአንድነት ሲባል ህወሓትን እንዲቃወም፤ ተደራጅቶ ለሃሳብ የበላይነት ትግል መዘጋጀት እንዳለበት በመግለጽ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም