የሰቲት ሁመራ ግብርና ምርምር ማእከል 4 የጎመን ዝርያዎች በምርምር ማውጣቱን አስታወቀ

91

ሰቲት ሁመራ ሐምሌ 22 /2012 (ኢዜአ)  የሰቲት ሁመራ ግብርና ምርምር ማዕከል በፋብሪካ ተቀነባብረው ለውጭ ገበያ የሚውሉ አራት የጎመን ዝርያዎች በምርምር ማውጣቱን አስታወቀ ።

በሁመራ ግብርና ምርምር ማዕከል የስነ ማዳቀልና ስነ ዝርያ ተመራማሪ አቶ ይርጋ በላይ ለኢዜአ እንደገለፁት በምርምር የወጡት የጎመን ዝርያዎች ''ባሚያ፣ጅርጅር፣መለኩያና ዋይካ'' የሚል ስያሜ ተሰጥቶአቸዋል ።

የጎመን ዝርያዎቹ ከምግብነት ባለፈ በፋብሪካ ተቀነባብረው ወደ ዓለም ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ  ምንጭ ሆነው ማገልገል የሚችሉ ናቸው ተብሏል ።

ላለፉት ሶስት ዓመታት ምርምር የተደረገባቸው የጎመን ዝርያዎች ውጤታማ ሆነው በመገኘታቸው ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተመራማሪው ተናግረዋል ።

በተለይ “ባሚያ” የተባለው የጎመን ዘርያ በ55 ቀናት ውስጥ የሚደርስና  በአንድ ሄክታር መሬት ከ260 ኩንታል በላይ ምርት የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል ።

የጎመን ዝርያው የቅባት ይዘት ያለው በመሆኑ ደርቆና በማሽን ተፈጭቶ ለውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ነው ብለዋል ።

ሌሎች ዝርያዎችም ከምግብነት ባለፈ በአግሮ ፕሮሴሲንግ  ደረጃ ተቀነባብረው ለውጭ ገበያ እንዲላኩ  እየተሰራ መሆኑን ተመራማሪው ተናግረዋል።

ዝርያዎቹ በሔክታር እስከ 200 ኩንታል የሚደርስ ምርት የመስጠት አቅም እንዳላቸውም ከተመራማሪው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

ዝርያዎቹ በአሁኑ ወቅት  በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ  በታህታይ አድያቦ ፣ቆላ ተምቤን ወርዒ ለኸና አላማጣ ወረዳዎች የማላመድና የማሰራጨት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰቲት ሁመራ ጤና ፅህፈት ቤት የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ አቶ ግርማይ በየነ እንደገለፁት ዝርያዎቹ በምግብ ይዘታቸው በሽታ የመከላከል አቅምን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል ።

“ ኪንታሮት ፣የስኳር በሽታ ፣የደም ግፊት፣ የጨጓራ ፣የሆድ ድርቀትና መሰል የጤና ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም የጤና ባለሙያው ገልፀዋል ።

በዞኑ የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ ብርሃነ ፍሳሃ እንደገለፁት ደግሞ ዝርያዎቹ ተቀባይነታቸው እየጨመረ በመምጣቱ በመስኖ በስፋት ለማምረት ለአርሶ አደሮች ስልጠና እየተሰጠ ነው ።

ሴት አርሶ አደር ለታይ ሓድጉ እንደተናገሩት ''ባሚያ'' የተባለ የጎመን ዝርያ ከምርምር ማእከሉ በነጻ ወስደው በማባዛት ላይ ይገኛሉ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም