የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን የመቆጣጠር ኃላፊነታችንን እንወጣለን--የምክር ቤቱ አባላት

68

ባህር ዳር ሐምሌ 22/2012 (ኢዜአ) በመንግስት የተመደበው በጀት የህዝቡን የልማት ጥያቄ መሰረት በማድረግ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን   የመከታተልና መቆጣጠር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ። 

በባህርዳር  ከተማ ሲካሄድ የቆየው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ  ትናንት ማምሻውን ከመጠናቀቁ በፊት ለ2013 የስራ ዘመን  62 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት ማጽደቁን ኢዜአ  በወቅቱ ዘግቧል።

ይህን ተከትሎ ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ መሰረት ኃይሌ እንደገለፁት ለተያዘው የበጀት ዓመተ የህዝቡ የመልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ በጀት ተመድቧል።

የተመደበው በጀት ጊዜውን ጠብቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በየደረጃው ባለው አስፈፃሚ ጥንካሬ ልክ የሚወሰን መሆኑን ተናግረዋል።

"ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የተመደበው በጀት በወቅቱ ለታለመለት ዓላማ  እንዲውል ለማድረግም የጋራ አቋም ይዟል "ብለዋል።

በጀቱ ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች መመለስ በሚያስችል አግባብ በቁጠባ ለልማት ስራዎች እንዲውልም አስፈፃሚውን በየጊዜው የመከታተልና መቆጣጠር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።

አስፈጻሚው አካላትም በርካታ የልማት ጥያቄ ቢኖርም የተገኘውን ውስን በጀት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የልማት ስራዎች በማዋል ህዝባዊ አደራቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

"የተመደበው በጀት በተለይ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የጎላ ድርሻ እንዲይዝ በምክር ቤቱ ተገምግሟል "ያሉት ደግሞ  ሌላም የምክር ቤቱ አባል አቶ አዲስ እርቄ ናቸው።

የምክር ቤት አባላት በተያዘው የበጀት ዓመት  ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሳቸውን አስታውቀዋል።

የተመደበውን በጀት የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች በሚመልሱና የክልሉን ምጣኔ ሃበት አቅም የሚያሳድጉ የመንገድ፣ መስኖ፣ ውሃ እና መሰል ፕሮጀክቶችን በላቀ ብቃት መፈፀም ይገባል ብለዋል።

ለስኬታማነቱም አስፈፃሚው አካል ከለዘብተኝነት ተላቆ ለህዝብ ጥያቄዎችን ፈጥኖ መልስ ለመስጠት መረባረብ እንዳለበትም አመልክተዋል።

"ምክር ቤቱ ጠንካራ አቅጣጫ አስቀምጧል "የሉት አቶ አዲስ እርሳቸውም አስፈጻሚውን አካል ተከታትለው  በመቆጣጠር የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጥላሁን መሐሪ  በበኩላቸው የ2013 የስራ ዘመን በጀት  የህዝቡ መሰረታዊ ፍላጎቶች ተለይተው ሳይቀርቡ ወደ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች እንደማይለቀቅ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም በተለይ የካፒታል በጀት የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት በትክክል ሳይለይ ለወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ይለቀቅ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም የተነሳ ውስን የሆነው የካፒታል በጀት በስራ ዘመኑ መጨረሻ በብዙ ወረዳዎች ላይ ተመላሽ ሲሆን መቆየቱን ጠቅሰዋል።

አንዳንድ ወረዳዎች ደግሞ የካፒታል በጀትን ወደ ስራ ማስኬጃ ይቀየርልን ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር አውስተው ፤ ይህም ህዝቡ የሚፈልጋቸውን የመሰረተ ልማት አውታሮች ተለይተው ወደ ስራ ባለመግባታቸው እንደሆነ አመላክተዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት ለህዝብ የሚሰሩ የልማት ተግባራት ከወዲሁ ተለይተው ካለቀረቡ በስተቀር ለወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በጀት እንደማይለቀቅ አረጋግጠዋል።

የወረዳና ከተማ አስተዳደር አመራሮች ይህንን በመገንዘበ በሚያከናወኑት  ስራዎች ዙሪያ ህዝብን በማወያየት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ለይተው እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የካፒታል በጀት በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውልም የዞንና የወረዳ አመራሮች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግም  ዶክተር ጥላሁን አስታውቀዋል።

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችንና ዳኞችን ሹመት በማጽደቅ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም