የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ድጋፍ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ድጋፍ አገኘ
ደሴ ሀምሌ 22/2012 (ኢዜአ) በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የወሎ ተወላጆች ለደሴ ሪፈራል ሆስፒታል አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጋቸውን ሆስፒታሉ ገለፀ ፡፡
የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ የሱፍ እንደገለጹት በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የወሎ ተወላጆች የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ለማቃለል የሚያስችል ድጋፍ አድርገዋል ።
ድጋፉ የሰውነት ሙቀት መለኪያ፣ ኦክስጅን ኮንሴትሬተር፤ ሴፍቲ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የመሳሰሉትን ያካተተ ነው ።
ዛሬ በድጋፍ ከተገኙት መሳሪያዎች መካከል የተወሰኑት በገበያ ላይ በቀላሉ የማይገኙና ዋጋቸው ውድ በመሆኑ በሆስፒታሉ ስራ ላይ ጫና አሳድረው መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
የህክምና መሳሪያዎቹ የተሟላ ህክምና ለመስጠት የሚያግዙ በመሆናቸው ስራ አስኪያጁ ምስጋና አቅርበዋል ።
የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ በበኩላቸው ኮሮና የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ በአገር ውስጥና በውጭ ለሚኖሩ የወሎ ተወላጆች አካባቢያቸውን እንዲደግፉ ጥሪ ቀርቦ ነበር ።
በተደረገው ጥሪ መሰረትም የህክምና ቁሳቁስና የምግብ እህል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በቅርቡ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የወሎ ተወላጆች ከ500 ኩንታል በላይ የተለያየ የምግብ እህል ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ቀጣይ ሌሎች ድጋፎች ለማግኘትም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሱን ከወርርሽኙ እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡