ፍርድ ቤቱ በአቶ ሀምዛ አዳነ እና በጃዋር መሀመድ የግል ጠባቂዎች ላይ ተጨማሪ ስምንት ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

አዲስ አበባ  ሀምሌ 21/2012 (ኢዜአ)የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአቶ ሀምዛ አዳነ (ቦረና) እና በጃዋር መሀመድ የግል ጠባቂዎች ላይ ተጨማሪ ስምንት ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት እጃቸው አለበት ተብለው በተጠረጠሩት  አቶ ሀምዛ አዳነ (ቦረና) እና የጃዋር መሀመድ የግል ጠባቂዎች ላይ ፖሊስ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ስምንት ተጨማሪ ቀናት ተፈቅዶለታል።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ባለፉት 12 ቀናት አከናወንኩ ያላቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርቧል።

በዚሁ መሰረት በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ቀናት የተጠርጣሪዎችንና የምስክሮችን ቃል መቀበል እንዲሁም በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት የማጣራት ተግባራት ማከናወኑንና ከመዝገብ ጋር ማያያዙን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

መርማሪ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት 1ኛ ተከሳሽ አቶ ሀምዛ አዳነ የብሔርና የሃይማኖት ግጭት እንዲቀሰቀስ በተለያዩ ሚዲያዎች ጥሪ ሲያስተላልፉ እንደነበር የድምጽና የምስል ማስረጃ ማሰባሰቡን ገልጿል።

የጃዋር መሀመድ የግል ጠባቂዎች በሆኑት የዓለምወርቅ አሰፋ፣ ታምራት ሁሴን፣ ሰበቆ ቃቆ፣ ኬኒ ዱመቻ፣ ዳዊት አብደታ፣ በሽር ሁሴን፣ ቦጋለ ድሪብሳ እና ጌቱ ተረፈ ላይ አግኝቸዋለው ያለውን ማስረጃም ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

በዚህ መሰረት የሟች አስክሬን ወደ አምቦ እየተጓዘ ባለበት ወቅት ቡራዩ ኬላ ላይ በማስገደድ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ በማድረግ በተፈጠረው ሁከት እና ግርግር የሰው ህይወት መጥፋቱን እና የአካል ጉዳት መድረሱን በምርመራ ማረጋገጡን መርማሪ ፖሊስ አብራርቷል።

ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት ተጠርጣሪዎቹ የአቶ ሃጫሉ ሁንዴሳን አስከሬን ጠልፈው ወደ ኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ባመጡበት ወቅት በተኮሱት ጥይት ለአንድ የኦሮሚያ ፖሊስ ህይወት ማለፍና 3 አባላት ላይ የአካል ጉዳት በማድረስ ወንጀል እንደጠረጠራቸው ገልጿል።

በቡራዩ በደረሰ ጉዳት የአራት ሰው ህይወት መጥፋቱንና አራት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እንዲሁም ሰባት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት እንደወደመ በማስረጃ ማረጋገጡን ገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የ14 ሰዎች ህይወት እንዲጠፋ በማድረግ እና 166 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንዲወድም ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሷል።

በተለያየ አካባቢ ሁከት እንዲነሳ የስልክ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተከትሎ መልዕክት የተቀበሉ ሰዎች ያደረሱትን ጉዳት እያጣራ እንደሚገኝም ፖሊስ አስረድቷል።

ከተጠርጣሪዎቹ ህገወጥ የጦር መሳሪያ እና የሬዲዮ መገናኛ በኢግዚቢትነት መያዙን እና ሁከትና ብጥብጥ እንዲባባስ መንገድ እንዲዘጋ ሲያስተባበሩ እንደነበር አንስቷል።

በክልል የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ 17 ቡድን መንቀሳቀሱን ገልጾ፤ የቡድኑን ውጤት እየተጠባበቀ እንደሚገኝም አመልክቷል።

ቀሪ የምርመራ ስራዎች እንዳሉት ያመለከተው መርማሪ ፖሊስ፤ ቀሪ ምስክር መስማትና ሽጉጦችን ለፎረንሲክ ምርመራ ልኮ ውጤት እየጠበቀ እንደሚገኝ ጠቅሷል።

በንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በደብዳቤ ጠይቆ ከተቋማት ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጾ ተጨማሪ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለማሰባሰብ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በወንጀል ድርጊት የጠረጠራቸው አቶ ሀምዛ አዳነ (ቦረና) እና የጃዋር መሀመድ የግል ጠባቂዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል እኛን አይመለከተንም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል

በተለይም ሀምዛ አዳነ ጋዜጠኛና አክቲቪስት መሆናቸውን ጠቅሰው ህገ መንግስቱ በፈቀደልኝ በህጋዊ መንገድ ነው ሀሳቤን ያራመድኩት በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የባንክ አካውንታቸው መታገዱን በመግለጽ በስራቸው ድርጅት ያላቸው በመሆኑ የግብር መክፈያ ወቅቱ ሳያልፍ እንዲከፍሉ የዋስ መብት እንዲፈቀድላቸው አልያም ደግሞ ውክልና መስጠት እንዲችሉ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል።

የጃዋር መሀመድ የግል ጠባቂዎች ደግሞ ምግብ ከውጪ እንዳያስገቡ መከልከላቸውን፣ ቅያሪ ልብስ ማግኘት አለመቻላቸውን እንዲሁም ቤተሰብ በስልክም ሆነ በአካል ሊያገኙ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በደመወዝ የሚተዳደሩ በመሆኑ የባንክ ሒሳብ ቁጥራቸው መታገዱ ቤተሰቦቻቸው ለችግር እንዲዳረጉ ማድረጉን ገልፀዋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ያቀረበው ተጨማሪ 14 ቀናት የሚወስድ የምርመራ ጊዜ አለመኖሩን ገልጸዋል።

ደንበኛቸው ላይ ፖሊስ ያቀረበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ደንበኛቸው የዋስ መብታቸው ተጠብቆ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ጠበቆች ደንበኛቸውን እንደልባቸው ለማግኘት እንደተቸገሩ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪዎቹ  የተጠረጠሩበት ወንጀል ስፋት ያለውና ውስብስብ መሆኑን ገልጿል።

የምርመራ ስራውን በፍጥነት ለመጨረስ እየተሰራ ቢሆንም በየአካባቢው የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት ጊዜ የሚወስድ መሆኑን አስረድቷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በሳምንት ሦስት ቀን ከደንበኛቸው ጋር እንዲገናኙ ፕሮግራም ቢወጣም ጠበቆች በተናጠል በመሄድ ፕሮግራሙን እያከበሩ እንዳልሆነ ገልጾ፤ በፕሮግራሙ መሰረት መስተናገድ ካልቻሉ ማጣራት አድርጎ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጧል።

ግራ ቀኙን ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ ቀደም የተሰጠውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በአግባቡ ማከናወኑን አይቷል።

ከወንጀሉ ስፋትና ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በመግለጽ ተጨማሪ ስምንት ቀናት በመፍቀድ ለሐምሌ 29 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪና ጠበቆች ከቤተሰብ ጋር በስልክ እንዲገናኙ በተመለከተ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ላቀረቡት አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ እንዲያስፈጽም እና ለፍርድ ቤትም እንዲያቀርብ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በተጨማሪም አቶ ሀምዛ ቦረና ህጋዊ ውክልና መስጠት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንዲመቻችላቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም