በአረንጓዴ አሻራ ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተተክሏል

88

አዲስ አበባ  ሀምሌ 21/2012 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በጉለሌ የእጽዋት ማዕከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መንግስትና ህዝብ በጣም ወሳኝ በሚባሉ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንኛው ጉዳይ መሆኑንና የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ የድል ብስራት እንደሆነ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት ባለፈው ዓመት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በስፋት እየተሄደበት መሆኑንም አቶ ንጉሱ አመልክተዋል።

"ባለፈው ዓመት ከተተከለው 4 ቢሊዮን ችግኝ ተሞክሮ በመውሰድ ለዘንድሮው ዓመት አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ የችግኝ ተከላው እየተከናወነ ነው" ብለዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለመትከል ከታቀደው 5 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ እስካሁን ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን ነው አቶ ንጉሱ የገለጹት።

መገናኛ ብዙሃን የችግኝ ተከላን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው በመስራት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የጉለሌ እጽዋት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ስለሺ ደገፋ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች ችግኝ እንደተከሉት ሁሉ የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃኑ አመራሮች በበኩላቸው የተከሏቸውን ችግኞች በመንከባከብ አርአያ የሚሆን ተግባር እንደሚፈጽሙ ተናግረዋል።

የተከልነው ችግኝ መንከባከብ በማስፈለጉ የህዝብ  ንቅናቄው እስከመጨረሻው እንዲሄድ ሚዲያ ወሳኝ ሚና አለው የሚሉት አቶ ብሩክ ከበደ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡

የአረንጓዴ አሻራ አካል  በመሆናችን እና አገራችን  የሕዳሴውን  ግድቡ እየገነባች ባለችበት አጋጣሚ የአካባቢ ጥበቃ መሰራቱ ጉልህ ድርሻ እንዳለው የሚያስረዱት ደግሞ  የዋልታ ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ንጉሴ መሸሻ ናቸው፡፡

እንደ ሃገር ብዙ የጋራ ጉዳዮች አሉብን የሰላም ጉዳይ አንዱ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ  አቶ ሰይፈ ደርቤ ሚዲያዎችም  ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመስራት  ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠርም እድል አላቸው ብለዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች ዛሬ ችግኝ የተከሉበት ቦታ መገናኛ ብዙሃን ብቻ ችግኝ እየተከሉ የሚንከባከቡበት የአትክልት ስፍራ እንደሚሆን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም