በጎንደር ከተማ በህገ ወጥ የሲሚንቶ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

163

ጎንደር፤ ሃምሌ 21/2012(ኢዜአ)በጎንደር የከተማ ሲሚንቶን በህገ ወጥ መንገድ በመደበቅና በናረ ዋጋ በመሸጥ ተግባር ተሰማርተው የተገኙ 11 ነጋዴዎች መደብሮቻቸው እንዲታሸግ መደረጉን የከተማው ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

መምሪያው ሰሞኑን ባካሄደው የክትትልና ቁጥጥር ስራበከተማው  በህገ-ወጥ መንገድ  በድብቅ የተከማቸ ሁለት ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ ተገኝቷል ።  

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ተስፋ መኮንን ለኢዜአ እንደተናገሩት መደብሮቹ የታሸጉት የሲሚንቶ ምርትን በህገ ወጥ መንገድ አከማችተው በመያዝ ሰው ሰራሽ የገበያ  እጥረት  በመፍጠር  በከፍተኛ ዋጋ ሲሸጡ በመገኘታቸው ነው።

ነጋዴዎቹ አንድ ኩንታል ሲሚኒንቶ በ800 ብር ሂሳብ በመሸጥ በከተማው በሚካሄደው የግንባታ እንቅስቃሴ ላይ ችግር ሲፈጥሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የሲሚንቶ ግብይትንና የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረትም ከሁለት ሺህ  ኩንታል  በላይ ሲሚንቶ በግለሰቦች መኖሪያ ቤትና በተቋማት ጭምር በድብቅ  ተከማችቶ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

በድበቅ ተከማችቶ የተያዘው ሲሚንቶም ንግድ ሚኒስቴር ባወጣው የዋጋ ተመን መሰረት በቤት ግንባታ ለተሰማሩ ግለሰቦችና ማህበራት ኩንታሉን በ430 ብር ሂሳብ መሸጡን ተናግረዋል።

ሲሚንቶን አለአግባብ በማከማቸት  በናረ ዋጋ  ሲሸጡ የተገኙትን ግለሰቦች በፖሊስ  በኩል በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ በማድረግ በንግድ ህጉ መሰረት ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑንም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

መምሪያው የሲሚንቶ ዋጋን በማረጋጋት ጤናማ የግብይት ስርአት እንዲፈጠር ለማድረግም ለሲሚንቶ ፈላጊዎች የኩፖን ስርአት በመዘርጋት ባለፈው ወር ብቻ 28 ሺህ ኩንታል  ሲሚንቶ እንዲሰራጭ አድርጓል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ በከተማው የተፈጠረውን የሲሚንቶ ዋጋ ንረትና የአቅርቦት ችግር  የሲሚንቶ ዋጋ በኩንታል ከ400 ብር ወደ 800 ብር ገብቷል ያሉት ደግሞ በቤት ግንባታ  የተሰማሩት አቶ ማሩ ቸርነት ናቸው፡፡

ነጋዴዎቹ ከደላሎች ጋር በመመሳጠር ከንግድ መደብሮቻቸው ውጪ በሆነ መንገድ  በድብቅ በየሰፈሩ ሲሚንቶን በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ህገ-ወጥ ንግድ  ላይ  እንደተሰማሩም  ተናግረዋል፡፡

በሲሚንቶ ዋጋ መወደድ ሳቢያ በክረምቱ የጀመርኩትን ግንባታ ለማቋረጥ ተገድጃለሁ  ያሉት ሌላው በከተማው በህንጻ ግንባታ የተሰማሩት አቶ ሲሳይ በፈቃዱ ናቸው፡፡

መንግስት በሲሚንቶ ምርት ላይ ዋጋ ቢተምንም ነጋዴዎች ተመኑን አክብረው እየሸጡ  አይደለም ያሉት አቶ ሲሳይ፤ የዋጋ ንረቱንና የአቅርቦት ችግሩን በመፍታት በኩል  የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በጎንደር ከተማ የንግድ ፈቃድ አውጥተው በሲሚንቶ የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ከ50 በላይ የጅምላና የችርቻሮ ነጋዴዎች መኖራቸውን ከመምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም