“የበላይነትን የለመደ እኩል ሁን ስትለው የተዋረደ ይመስለዋል”... ታዬ ደንደኣ

107

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2012 (ኢዜአ) አንድ ጊዜ የበላይነትን የለመደ አካል እኩል ሁን ሲባል የተዋረደ ይመስለዋል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደኣ አመለከቱ።

የህወሓት ጥገኛ ቡድን በሴራ ፖለቲካ የተካነ ስለመሆኑም የቀደሙ ታሪኮቹ ህያው ምስክሮች እንደሆኑ አስታውቀዋል ።

አቶ ታዬ ደንደኣ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤አሁንም ድረስ ምናልባትም በሚዲያዎች እንደሚሰማው ህወሃቶች እኛ በታሪክ ካለን አስተዋጽኦ አንጻር የተለየና የበለጠ ቦታ፤ስልጣንና ኢኮኖሚ ይገባናል ብለው በግልጽ ያነሳሉ።

ከዚህ ባለፈም በዚህ አገር ውስጥ በአንድ በኩል የተዘረፉና የተሰረቁ በርካታ ነገሮች አሉ፤ እናም ይሄ ለውጥ መሰረቱን ይዞ በትክክለኛው አቅጣጫ የሚዘልቅ ከሆነ ምናልባትም ነገ ተጠያቂነት ይመጣል የሚል ስጋትም አለባቸው ብለዋል።

እነዚህ ሃይሎች ያለፈውን ትተን እሱ ስለማይጠቅመን መልካም ነገሮችን አጎልብተን የተበላሹትን ለማስተካከል ከዚህ ጀምረን እንስራ፤ የይቅርታ መንገድ እንከተል የሚለውንም ለማመን አልፈለጉም የሚሉት አቶ ታዬ፣ ለማመን ያልፈለጉት ደግሞ እነርሱ ስለማይታመኑ ሁሉም እንደዛው ስለሚመስላቸው ነው ብለዋል።

"እነርሱ በአፋቸው የሚሉት ሌላ፤ በልባቸው የያዙት ሌላ ስለሆነ ሰው በቅንነት በዚህ ደረጃ ነው ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው ብሎ ቢነገር ከራሳቸው አንጻር ስለሚመነዝሩት ይሄንንም ሊያምኑ አልቻሉም። እየተጠራጠሩ ነው የመጡት" ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ታዬ ገለጻ፤ሁለተኛው ደግሞ እነርሱ ለዛ ክልልም ሆነ ማህበረሰብ በስሙ ነገዱበት እንጂ ለ27 ዓመታትም ሆነ ዛሬም ድረስ ያ ማህበረሰቡ ችግር ውስጥ ነው።

እነርሱ የሚሰሩት ለራሳቸው ስለሆነ ኢትዮጵያን እኛ ካልገዛናት፤ እኛ እንደፈለግን የማናደርጋት ከሆነች “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አይነት የአህያ ብሂል ኢትዮጵያን ወይ እኛ እንግዛት ካልሆነ ደግሞ ትጥፋ በሚል እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።

ከዚህ አንጻር መልሶ ስልጣን ለመቆጣጠር ፍላጎት አለ፤ ያ የማይሳካ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል የለባትም፤ እኛ የዛን ክልል ማህበረሰብ ለይተን እንገዛዋለን (እናስተዳድረዋለን ሳይሆን እንገዛዋለን ነው)፤ ሌላው ደግሞ ሀገር ሲቃጠል ዳር ሆነን እናያለን የሚል ስሜትስሜት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

‹‹ ይህ ሁሉ የሚሆነውም ለዚሁ ነው። የሴራ ፖለቲካ የህወሓት የተካነበት ነው። የሚያውቁት የሚናገሩትም ይሄንኑ ነው። ››ያሉት አቶ ታዬ፣ይህንንም በምሳሌ ሲያብራሩ ደርግ የመሬት ላራሹ ጥያቄን ሲመልስ ሁሉም የኢትዮጵያ አርሶአደሮች በአዎንታ የተቀበሉት መሆኑን ጠቅሰዋል።

‹‹ያንንም ትግራይ ላይም ጭሰኛ የነበሩ ዜጎች መሬት ሲያገኙ ደርግን ተቀብለውታል። ህወሓት መጀመሪያ መጥቶ ሲሰብካቸውም “እኛ መሬት አግኝተናል፤ ከዚህ በኋላ ሌላ አንፈልግም” ሲሏቸው፤ ሲያደርጉ የነበረው የደርግ ልብስ በመልበስ ደርግን መስለው ማታ ማታ እየገረፉና እየገደሉም ጭምር፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየመጡ ደርግ ገዳይ ነው፤ ደርግ እንደዚህ ነው፤ ይደፍራል፣ ይገድላል፣ ይገርፋል ብለው ይሰብኳቸው እንደነበር የሚያውቋቸው ይናገራሉ ሲሉ ያብራራሉ።

ከኢህአፓ ጋር የነበረውም ይሄው እንደሆነ ጠቅሰው፣አሲምባ ላይ በሴራ ነው በርካታ ሺዎች የኢህአፓ አባላት እንዲያልቁ የተደረገው ብለዋል።
እንደ አቶ ታዬ ገለጻ፤የሀውዜንም ሁኔታ ሰዎች የሚመለከቱት ያኔ ደርግ ከትግራይ ጥሎ ስለወጣ ከዚህ በኋላ የሰበካችሁን ትግራይን ነጻ እንድናውጣ ነበረ፤ ትግራይ ውስጥ ደርግ የለም፤ ስለዚህ ከዚህ በኋላ አንዘምትም በሚል ወታደሮቻቸው ጥያቄ ሲያነሱ በደርግም ውስጥ ከነበሯቸው ሰዎች ጋር በመቀናጀት በሴራ ያ እልቂት እንዲፈጠር አደረጉ።

ከዛም ደርግ ከምንጩ ካልጠፋ በስተቀር እዚህ ሰላም ልናገኝ አንችልም የሚል ሰበካ አመጡ። እናም ከመጀመሪያው አንስቶ በሴራ ነው እዚህ የደረሱት። አሁንም በሴራ እንጂ በትክክለኛ መንገድ በያዝነው አስተሳሰብ ልናሸንፍ እንችላለን ብለው አምነውም አያውቁም ነው ያሉት
ይሄ ሴራ ባለፉት 27 ዓመታትም በኦሮሞና በአማራ መካከል በኢህአዴግ ውስጥም በነበሩት ብአዴንና ኦህዴድ ውስጥም፤ ከዛ ውጪም በልሂቃን መካከል መቃቃር እንዲኖር ሆን ተብሎ የተሰራና የተሰላ ስሌት ነበር ያሉት አቶ ታዬ፣ ያ ስሌት ደግሞ አማራና ኦሮሞ ሊታረቅ የማይችል ቅራኔ አላቸው የሚል መሆኑን ገልጸዋል።

ይሄንንም በመጽሐፍ ጭምር መጻፋቸውን ፣በሚዲያዎችና በጋዜጣም ብዙ ሰብከዋል ሲሉ መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም