ማራቶን ሞተርስ በኢትዮጵያ የተገጣጠማትን በኤሌክትሪክ የምትሰራ መኪና ይፋ አደረገ

225

አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2012(ኢዜአ) ማራቶን ሞተርስ ኢነጂነርንግ በኢትዮጵያ የተገጣጣመችና በኤሌክትሪክ ሃይል የምትሰራ "ሀይዳይ" መኪና ይፋ አደረገ። 

የመኪናው መመረት ኢትዮጵያ በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ፋይዳው የጎላ መሆኑም ተገልጿል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ሃይል በማመንጨት ረገድ ከፍተኛ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች በኢትዮጵያ መገጣጣም መጀመራቸው ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን አመላክተዋል።

የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዲጎለብት መንግስት አበክሮ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

"የጉዟችን መዳረሻ የኢትዮጵያ ብልጽግና ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አንጻር የሚገጥሙን ፈተናዎች ይበልጥ ያጠነክሩናል እንጂ አያቆሙንም ብለዋል።

የማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ የቦርድ ሊቀመንበር አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ እንዳለው መኪኖቹ በቀላሉ ቻርጅ ተደርገው የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

መኪኖቹ ገበያ ላይ ሲውሉ ለነዳጅ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ረገድ በጎ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።

በኢሌክትሪክ የሚሰራ መኪና ኢትዮጵያ ውስጥ መገጣጣም እንዲጀመር ከፍተኛውን 'ኢንሸቲቭ' የወሰዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሆናቸውንም ተናግሯል።

በስራ ውስጥ በሚገጥም ፈተና ተስፋ ቆርጦ መቆም አይገባም ያለው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በቅርቡ በባቱና ሻሸመኔ በሚገኙት ሪዞርቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ከመንገዳችን አያሰናክለንም ብሏል።

በሚቀጠለው ነሃሴ ወር በአዳማ ከተማ ትልቅ ሪዞርት እንደሚያስመርቅም ተናግሯል።

በሌሎች አካባቢዎች የጀመራቸውን የኢንቨስትመንት ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል።

ከተመሰረተ አስር ዓመታትን ያስቆጠረው ማራቶን ሞተርስ የደቡብ ኮሪያው ግዙፍ የመኪና አምራች "ሃይዳይ' ምርቶችን ከወራት በፊት በኢትዮጵያ መገጣጠሙን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በወቅቱ ለእይታ የበቁት መኪኖች በነዳጅ የሚሰሩ የነበሩ ሲሆኑ አሁን ላይ ደግሞ በኤሌክትሪክ ሃይል የምትሰራዋን መኪና ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም