የአገር ሽማግሌዎች ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሙሉ አቅማቸው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ

81

አዲስ አበባ  (ኢዜአ) ሀምሌ 19/2012ዓም የአገር ሽማግሌዎች ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሙሉ አቅማቸውን አሟጠው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የሰላም አምባሳደር እና የአገር ሽማግሌው ሀጅ ሰኢድ አህመድ የአገር ሰላምና ደህንነትን አስመልክተው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

በእዚህም ሰላም ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ያለሰላም ውሎ መግባትም ሆነ የአገር አንድነትን ማቆየት እንደማይቻል ተናግረዋል።   

በአንድ አገር ውስጥ ሰላምን ለማስፈን የአገር ሽማግሌዎችና ታላላቅ አባቶች ሚናቸው የጎላ መሆኑን የጠቆሙት ሀጂ ሰኢድ፣ በየጊዜው የሚነሱ የሰላም እጦቶችን በማስቀረት በኩል የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በየአካባቢው ያሉ የአገር ሽማግሌዎችና ታላላቅ አባቶች ወደፊት መውጣትና ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለአገር ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለህዝቦች አብሮነት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የአገር ሽማግሌዎች አብሮነታቸውን እንዲያጠናክሩም ነው ሀጂ ሰኢድ የገለጹት፡፡

የሰላም አምባሳደሩና የአገር ሽማግሌው ሀጅ ሰኢድ ከ2010 ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ስለሰላምና የህዝቦች አብሮነት ሲሰብኩ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ በቀጣይም በሰላም ላይ የጀመሩትን ሥራ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ሌሎች የአገር ሽማግሌዎችም ለሰላም ሥራ ቅድሚያ ሰጥተው በመንቀሳቀስ የአገርን ሰላምና የህዝቦችን አብሮነት እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል::

ሀጂ ሰኢድ እንዳሉት ከአገር ሽማግሌዎች የሚጠበቀው ወጣቶችን በየጊዜው ከመምከርና ትክክለኛውን መንገድ ከማሳየት ባለፈ ያልተገቡ ሥራዎችን ሲሰሩ መገሰጽና ማረም ነው።

"እኛ የአገር ሽማግሌዎች ልጆቻችንን ከፊት አድርገን ከኋላ እኛ መከተልና አካሄዳቸውን ማሳየት ይኖርብናል" ሲሉም ተናግረዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም