ህብረተሰቡ የንግስ በዓልን ሲያከብር እራሱን ከኮሮና በመጠበቅ ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ የንግስ በዓልን ሲያከብር እራሱን ከኮሮና በመጠበቅ ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ
ሀዋሳ ሐምሌ 18/2012 (ኢዘአ) ህብረተሰቡን ዓመታዊ የቅዱስ ገብርኤል ንግስ በዓልን ሲያከብር እራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ።
የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነርና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል መሳፍንት ሙሉጌታ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ለህብረተሰቡ ደህንነት ሲባል የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ንግስ በዓልን የእምነቱ ተከታዮች በቤታቸው ሆነው እንዲያከብሩ ከቤተክርስቲያኗ አባቶች ጋር በተደረገ ውይይት ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ህብረተሰቡ ይህንን ተፈፃሚ በማድረግና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎችን በማክበር ራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅረበዋል።
የህብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ክልል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር በጋራ ሆኖ ከመንቀሳቀስ ተቆጥቦ ወረርሽኙን ለመከላከል ጥንቃቄ በማድረግ የበኩሉን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አሰተላልፈዋል።
የሀዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙንጣሻ ብርሀኑ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልፀው በተለይ በከተማዋ የበሽታው ስርጭት እየተስፋፋ መምጣቱን አስታውቀዋል።
በከተማዋ እስካሁን 63 ሰዎች በበሽታው መያዘቻውን ጠቅሰው የስርጭቱ መጠን እየጨመረ ነው ብለዋል።
ህብረተሰብም ይህንን በመረዳት ከወትሮው በተለየ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።