የየካ ክፍለከተማ አመራሮች የቦንድ ግዢ ፈጸሙ

41

አዲስ አበባ ሐምሌ 17/2012 (ኢዜአ) በየካ ክፍለ ከተማ ያሉ የወረዳ አመራሮች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ ፈፀሙ። 

የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ለገሰ እንዳሉት በክፍለ ከተማው ስር በሚገኙ 14 ወረዳዎች ያሉ ከ450 በላይ አመራሮች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለግድቡ ግንባታ እንዲውል በማድረጋቸው ነው የቦንድ ግዢው የተፈፀመው።

አባይ ቀደም ባሉት ጊዜያት “አባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” እየተባለ በቁጭት ሲነገርለት የነበረ ቢሆንም አሁን ባለው ትውልድ ግን ግድቡ ተገንብቶ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው የገለፁት።  

የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ‘ግድቡ ተሽጧል’ እየተባለ ሲነዛ የነበረው የሀሰት ወሬ መሰረተቢስ መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል።

ግድቡ እዚህ ደረጃ ላይ በመድረሱ የክፍለከተማው አመራሮች በመደሰታቸው ይህን የቦንድ ግዢ መፈፀማቸውን ገልፀው ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

የየካ ክፍለከተማ የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኪዳነማርያም አለማየሁ በበኩላቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ እዚህ ደረጃ መድረስና የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት ታሪክ የተሰራበት ዳግም አድዋ ነው ብለውታል።

ፅህፈት ቤቱ የውሃ ሙሌቱን ተከተሎ ለአመራሮች ባደረገው ንቅናቄ ድጋፉ መደረጉን ተናግረው በቀጣዮቹ የክረምት ወራት ኀብረተሰቡን በማስተባበር 21 ሚሊዮን ብር ሃብት ለማሰባሰብ መታቀዱንም ገልፀዋል።

ኀብረተሰቡ ሰሞኑን በግድቡ ውሃ መያዝ የተፈጠረውን መነቃቃት በመቀጠል ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድጋፉን እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።