የእርሻ ስራን በቆላማ አካባቢዎችም በማልማት በምግብ ራስ የመቻል ጥረትን ማረጋገጥ ይገባል

74

''የእርሻ ስራን በደጋማ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በቆላማ አካባቢዎችም በማልማት በምግብ ራስ የመቻል ጥረትን ማረጋገጥ ይገባል'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዛሬው ዕለት በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በተካሄደ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰመራ ከተማ ችግኝ ከተከሉ በኋላ በክልሉ ዱብቲ ወረዳ በመስኖ እየለማ ያለ የእርሻ ማሳን ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉብኝታቸው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት፤ ዛሬ በአፋር ክልል የተገኙት የእርሻ ስራውን ለመቃኘትና የአረንጓዴ አሻራቸውን ለማሳረፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመስኖ የለማውን የእርሻ ሥራ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት መሬቱ ለረዥም ዓመታት ጥቅም ላይ ሳይውል ቆይቶ በአሁኑ ወቅት እየለማ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ በረሃማ አካባቢ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ የመስኖ ውሃ በመጠቀም በዓመት ለሶስት ጊዜ እንደተመረተበት አብራርተዋል።

በመስኖ እርሻው ጥጥ፣ ስንዴ እና ለከብት መኖ የሚውል ሳር አይነት ምርቶችን ማምረት ስለመቻሉ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የእርሻ ሥራ በደጋማ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በቆላማ አካባቢዎችም ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ ለከብት መኖ የሚውለውን ምርት በብዛት በማምረት ለአገር ውስጥ ከብት እርባታ ማዋል እንደሚቻል እና አለፍ ሲልም ወደ ውጪ በመላክ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

ከዚህ አኳያ የአሰብ እና ጅቡቲ ወደቦች ለአካባቢው በጣም ቀረቤታ ያላቸው በመሆኑ ምርቶቹን በቀላሉ ወደውጭ በመላክ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻልም ጨምረው አስገንዝበዋል።

በበርሃማ አካባቢዎች ውሃ በየቦታው በመያዝ በተለይም በአፋርና ሶማሌ ክልሎች ላይ የእርሻ ስራዎችን በስፋት በመስራት ስንዴን ከውጪ ማምጣት ለማስቆም የሚችል አቅም እንዳለ ገልጸዋል።

ይህን ሥራ እውን ለማድረግ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ዛፍ መትከል እንደሚገባ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ''ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ቀደም በተገኙ ድሎች ሳንኩራራ አዳዲስ ዘላቂ ጥቅም የሚያረጋገግጡ ድሎች ለማስመዝገብ ታጥቀን መነሳት አለብን'' ብለዋል።

''ይህን ሁሉ ሀብት ይዞ ሳይሠራበት ከሌላው መለመን አይገባም'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ''ልመናን የምንጠየፍ እና ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የምንተርፍ መሆኑን በስራ ማሳየት ይገባል'' ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን በበጎ ፈቃድ ወጣ  እያሉ አገራቸውን በመጎብኘት በየክልሉ ያለውን አቅም ሊያዩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያዊያን ትኩረታቸውን አገራቸውን በማልማት ላይ በማድረግ ሲፈልጉ 'እንሰጣለን' ሲፈልጉ 'እንከለክላለን' እያሉ ከሚያስፈራሩ ሀይሎች ነፃ ለመውጣት ተባብሮ መስራት እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ ሁሉም መትጋት እንዳለበት አሳስበዋል።

እያንዳንዱ ዜጋ አገሪቱ ትልቅ አቅም እንዳላት ተረድቶ ወደ ሥራ እንዲሠማራ እና እንዲተባበር ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንሥራ በገንዘብ፣ ጉልበት እና እውቀት መደገፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም