በጤና ተቋማት ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ተናገሩ

1021

ደብረ ብርሃን ሐምሌ 3/2010 የጤና ተቋማት ለጤና መድህን አባላት የሚሰጡት የሕክምና አገልግሎት በመሻሻሉ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት ችለናል ሲሉ በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

በአንጎለላና ጠራ ወረዳ የአዳዲ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሚሊዮን አበራ ቀደም ሲል ለጤና መድህን አባላት ይሰጥ የነበረው የህክምና አገልግሎት ከፍተኛ መጉላላት የነበረበት እንደነበር አስታውሰዋል።

መድኃኒት የለም፣ በግላችሁ ከፍላችሁ ገንዘቡ ይተካላችኋል በሚሉና በመሳሰሉት ችግሮች መጉላላት ይደርስባቸው እንደነበር ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ችግሮች መወገዳቸውን ተናግረዋል።

በቅርቡ በጫጫ ጤና ጣቢያ ሄደው በጤና መድን መታወቂያ ካርዳቸው ፈጣን የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቁመው፣ በአንድ ቀን ብቻ 800 ብር የሕክምና ወጪያቸው እንደተወራረደላቸው አመልክተዋል።

በወረዳው የቡራ ጦጦሴ ቀበሌ ነዋሪ ቄስ ደረሰ ነገሰ ቀደም ሲል ለሕክምና ወደ ጤና ተቋም ሲሄዱ በግል ከፍለው ለሚታከሙ ቅድሚያ አገልግሎት እየተሰጠ የጤና መድን አባላት እንጉላላ ነበር ብለዋል።

በተለያዩ የውይይት መድረኮች ቅሬታቸውን ከማንሳት ባለፈ ለጤና ባለሙያዎችና ለአመራሩ አስተያየት በመስጠጥ አገልግሎቱ እንዲሻሻል ሲጠይቁ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

“በዚህም በአሁኑ ወቅት በጤና ተቋማት ቀልጣፋ አገልግሎት ከማግኘታችን ባለፈ ከጤና ጣቢያና ሆስፒታሎች የማናገኛቸውን መድኃኒቶች ከውጪ ገዝተን ወጪውን በደረሰኝ ማወራረድ ችለናል” ብለዋል፡፡

በደብረ ብርሃን ከተማ የቀበሌ 04 ነዋሪ አቶ አዲስ ለማ ለሰባት ቤተሰባቸው በዓመት 290 ብር ብቻ ለጤና መድህን አግልግሎት በመክፈል የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ብቻ በጤና ተቋም ከአራት ጊዜ በላይ የሕክምና አገልግሎት በማግኘት ከ2 ሺህ 150 ብር በላይ ወጪ ማስቀረታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን ጤና መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ አዝማቸው ደበበ በበኩላቸው ከአባላት ይነሱ የነበሩት ቅሬታዎች አግባብ እንደነበሩ ገልጸዋል።

በተነሱት ቅሬታዎች ላይ ከዞን እስከ ቀበሌ በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች የተገኙ ግብዓቶችን በመቀመር አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ከ275 ሺህ በላይ የጤና መድን አባላትን ማፍራት እንደተቻለ የጠቀሱት ባለሙያው፣ በአብዛኛው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እየተከሰተ ያለው ከጤና ባለሙያዎች የአስተሳሰብ ክፍተት መሆኑን ገልጸዋል።

የጤና መድህን አባላት አገልግሎት የሚያገኙበትን ካርድ ይዘው አለመምጣትም ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳያገኙ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ችግሩን በመነጋገር መፍታት እንደተቻለ ገልጸው፣ “በቀጣይም የተሻለ አገልግሎት መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

በዚህ ዓመት ከአባላት መዋጮ 39 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን አመልክተው፣ በተሰበሰበው ገንዘብ 19 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ 384 ሺህ ሰዎች የህክምና አገልግሎት አንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል።