አገር አቀፍ የቤቶች አስተዳድር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

205
አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2010 በከተሞች የሚስተዋለውን የቤቶች እጥረት የሚፈታ አገር አቀፍ የቤቶች አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር አባይ ለኢዜአ እንዳሉት መንግስት ሁሉንም ሰው የቤት ባለቤት ማድረግ ባይችልም በኪራይም ቢሆን ነዋሪዎች መጠሊያ እንዲያገኙ እየተሰራ ነው። ከዚህ በፊት የተለያዩ የቤቶች ፕሮግራሞች ተቀርጸው በርካታ ቤቶች ቢገነቡም በከተሞች ካለው የቤት ፍላጎት ጋር ሊጣጣም አለመቻሉን አስታውሰዋል። የቤቶች ግንባታን ለማሳደግ መንግስት ብቻውን ቤት እየገነባ የሚሰጥበት አሰራር አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸው፤ ባለሀብቱም እንዲሳተፍበት ህብረተሰቡም በቁጠባ እየተደራጀ የቤት ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ስለሆነም በከተሞች የሚስተዋለውን አንገብጋቢ የቤቶች ጉዳይ በሕግ ማዕቀፍ ለመምራት የቤት አስተዳድር አዋጅና የቤቶች ልማትና ግብይት አዋጅ የተሰኙ ሁለት ረቂቅ አዋጆች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ስለሆነም በቀጣይ ትኩረት የተደረገበት የኪራይ ውልና የጋራ መኖሪያ ቤቶች አስተዳድርን በተመለከተ 'የቤት አስተዳድር አዋጅ' የሚል ረቂቅ የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ረቂቁ ታይቶና በአከራይና ተከራይ እስከታች አስተያይት ተሰጥቶበት በሕብረተሰቡ ዘንድ ጠቃሚ ከሆነ እንደሚጸድቅ ተናግረዋል። የኪራይ ውልን በተመለከተ ኪራዩ በምን ውል ነው የሚተዳደረው? የሚለውን እንጂ ዋጋውን የሚተምን እንዳልሆነ ገልጸው፤ "የዋጋ ጉዳይ ራሱን የቻለ ጥናት ያስፈልገዋል" ብለዋል። በሌላ በኩል 'ቤት እንዴትና በማን ይለማል' የሚለውን አሰራር የያዘ የቤት ልማትና ግብይት ልማት ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ግንባታዎቹ በአገር ውስጥ ወይስ በውጭ ተቋራጮች ይካሄዳሉ? በሚለው ጉዳይ ላይ የአገር ውስጥ ተቋራጮች አቅም ማሳደግና ከፍተኛ የቤት ፍላጎት ሁለት የሚጋጩ ጉዳዮች እንደሆኑ ጠቁመዋል። የአገር ውስጥ ተቋራጮች አቅምን ለማሳደግ አቅም ያላቸው ተቋራጮች ካሉ ቅደሚያ እንደሚሰጥ ገልጸው፤ ነገር ግን አቅም ካነሳቸውና የቤት ፍላጎቱን ማሟላት ካልቻሉ የውጭ ተቋራጮች ተሳትፎ እንደማይገደብ ተናግረዋል። ረቂቅ አዋጆቹ በመንግስት ውሳኔ ብቻ ሳይሆን የአከራይና ተከራይ ሁለት ተዋዋዮች ፍላጎትና አስተያይት ታክሎበት የሕብረተሰቡ ፍላጎት ከሆነ ታይቶ ይጸድቃል። የረቂቅ አዋጆቹ የጥናት ሰነድ ተጠናቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን የገለጹት አቶ ጃንጥራር፤ አስፈላጊው ውይይት ተደርጎበት በመጭው መስከረም ወር እንደሚታይ አረጋግጠዋል። ከውይይቶች በኋላም ዓለም ላይ ካለው ልምድ በመነሳት የሚኒስተሮች ምክር ቤት መክሮበት ወደ ፓርላማ ሂዶ እንደሚጸድቅ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የግሉ ተቋም የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ እንደሚደረግ ባሳለፍነው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም