ከሶዶ ማረሚያ ተቋም የሚወጣው የፍሳሽ ቆሻሻ ለጤና መታወክ እያጋለጣቸው መሆኑን ነዋሪዎች ገለፁ

1395

ሃዋሳ ሰኔ 3/2010 ከሶዶ ማረሚያ ተቋም የሚወጣው የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽና ቆሻሻ ለጤና መታወክና ለተለያዩ ችግሮች እያጋለጣቸው መሆኑን የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከማረሚያ ተቋሙ የሚወጣው የመፀዳጃ ቤት ቆሻሻ የጤና ችግር እያስከተለባቸው ነው፡፡

በሶዶ ከተማ የዋቶ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ኢሳያስ አሻ ከማረሚያ ተቋሙ የሚወጣው የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽና ቆሻሻ ላለፉት 10 ዓመታት አካባቢያቸውን ሲበክል መቆየቱን ገልፀዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክተው ለሚመለከተው አካል ቢያሳውቁም እስካሁን ምላሽ አላገኙም፡፡

ከመጸዳጃ ቤቱ በሚወጣው ፍሳሽ ምክንያትም በየጊዜ ለጤና መታወክ እየተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ቆሻሻው ለልጆቻቸውና ለራሳቸው ጤና ስጋት እንደሆነባቸው የገለፁት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ታምራት ወገሶ ናቸው፡፡

በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም ምላሽ እንዳላገኙና በግድየለሽነት ቆሻሻው ወደ ውጭ እንዲፈስ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከተቋሙ በሚለቀቀው የመጸዳጃ ቤት ቆሻሻ ሽታ ምክንያት ቤታቸው መቀመጥ እንዳልቻሉ የገለፁት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ቅድስት ዳታ ናቸው፡፡

ለረዢም ጊዜ የቆየው ይኸው ችግር መፍትሄ ባለማግኘቱ ለልጆቻቸውና ለራሳቸው ጤና ጠንቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፍሳሹ ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ ከጎርፍ መውረጃ ቦይ ውስጥ ስለሚፈስ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው ተቋሙ ኃላፊነቱን ወስዶ ቢንቀሳቀስ የአካባቢው ህብረተሰብ ተቀናጅቶ ለመስራት ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሶዶ ከተማ ጤና ፅህፈት ቤት ሃለፊ አቶ መርዕድ ተስፋዬ ”ችግሩ በጤና ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከፍተኛ ሆኖ ሳለ ተገቢውን ምላሽ ላለመስጠታች ኃላፊነት እንወስዳለን” ብለዋል፡፡

የማረሚያ ተቋሙ ረዳት ኮሚሽነር ሉቃስ ቴቃ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በ20 ሚሊዮን ብር አዲስ ማረሚያ ተቋም ለመገንባት በ2004 ግንባታ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

ግንባታው በሁለት ዓመት ተጠናቆ ችግሩን ይፈታዋል የሚል እቅድ  የነበራቸው ቢሆንም አዲሱ የማረሚያ ተቋም ግንባታ ፕሮጀክት ሳይሳካ መቅረቱ ችግሩ እልባት እንዳያገኝ አድርጎታል ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱን ግንበታ እንዲያከናውን የተሰጠው የደቡብ ክልል ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በአፈጻጻም አቅም ውስንነት ጉድለት በጅምር እንዳቆመው ገልጸዋል፡፡

ለህዝቡ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ፕሮጀክቱን ቀድሞ ከጀመረው የክልሉ ቤቶች ልማት ጋር የነበረውን ውል በማቋረጥ ከሶስት ወራት በፊት ለሌላ ስራ ተቋራጭ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡

ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ከክልሉ ማረሚያ ተቋም ኮሚሽን ጋር በመነጋገር የፍሳሽ ቆሻሻ ማስመጠጫ ማሽን በማስመጣት እንደሚያነሱ ገልጸዋል፡፡