በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የምርምር ስራዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደለም- ምሁራን

70
ሀዋሳ ግንቦት 1/2010 በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የምርምር ስራዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋሉ አለመሆናቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ "ህገ-መንግስታዊነትና መልካም አስተዳደር ቀጣይነት ላለው የሀገር ልማት" በሚል መሪ ቃል ትላንት አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡ የአውደ ጥናቱ ተሳታፊ ምሁራን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ አብዛኛው የምርምር ስራዎች መደርደሪያ ላይ ከመቀመጥ ባለፈ ጥቅም ላይ ሲውሉ አይታዩም። በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገቨርነንስ ልማት ጥናት ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ተካ እንደገለፁት በምርምር የሚገኙ ውጤቶች በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፖሊሲ አውጪ ተቋማት ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ዩኒቨርሲቲዎችም ወደ ተቋማቱ መቅረብ አለባቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ዮሀናን መልካሙ በበኩላቸው አንድ ጥናት ሲካሄድ ብዙ ወጪ ወጥቶበትና በርካታ የሰው ኃይል ተሳትፎበት ቢሆንም በምርምሩ የሚገኙትን ውጤቶች ወደ ተግባር ከመለወጥ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ጥናት በሚያደርገው ከፍተኛ ትምህርት ተቋምና በመንግስት ፖሊሲ አውጪዎች መካከል ያለው ግንኙነት የጠበቀ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በውጪ ሀገር የምርምር ተቋማት ለመንግስት የፖሊሲ ሀሳብ የሚሆን ግብዓት የሚሰጡ እንጂ ራሳቸውን ችለው የሚቀመጡ ደሴቶች አደሉም ያሉት አቶ ዮሀናን በሀገራችንም ይህ ሁኔታ መለመድ ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል ። በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግና ገቨርነንስ ኮሌጅ ዲን አቶ እድሉ ሾና እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው እስካሁን በርካታ ጥናትና ምርምሮችን አካሂዷል ። በተለይ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ተቋማት ጋር በመተባበር በዘርፉ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው በዩኒቨርሲቲው የሚሰሩና የጎላ ጠቀሜታ ያላቸው የምርምር ውጤቶች ታትመው ለተጠቃሚ እንዲደርሱ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል ። በማህበራዊ ሳይንስ መስክ ለሚደረጉ ጥናቶችና ምርምሮች የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን አቶ እድሉ ተናግረዋል ። አውደ ጥናትቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ መዘጋጀቱን አስረድተዋል ። ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አቶ አያኖ ባሪሶ በበኩላቸው የአውደ ጥናቱ ዋና አላማ በተመራማሪዎችና በመንግስት አካላት በኩል በህገ-መንግስታዊነትና መልካም አስተዳደር ዙሪያ ዕውቀትና ልምድ ለመለዋወጥ ነው፡፡ በተጨማሪም በጥናትና ምርምር ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍቶተችን በመለየት የሚፈቱበትን መንገድ ለመፈለግ የአውደ ጥናቱ አላማ መሆኑን አስረድተዋል ። ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት በህግና መልካም አስተዳደር ዙሪያ ያተኮሩ በ10 ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተሰሩ 19 ጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም