በደቡብ ወሎ የአንበጣ መንጋ ስጋት ፈጥሯል

54

ደሴ (ኢዜአ) ሀምሌ 15/2012  በደቡብ ወሎ ዞን በ20 ሺህ ሄክታር የግጦሽ ቦታና የለማ ሰብል ላይ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ  እየተከላከለ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው በተደጋጋሚ በመከሰት በሰብል ምርታማነትላይ ተፅእኖ እያሳደረ ይገኛል።

በዞኑ ከጥቅምት 2012  ዓ/ም ጀምሮ በተደጋጋሚ ተከሰቶ በ41 ሺህ  ሄክታር መሬት ላይ  በመኸር፤በመስኖና  በበልግ የለማ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰዋል፡፡

የአንበጣ መንጋው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በባህላዊ መንገድ በተደረገ የመከላከል ጥረት ከአካባቢው ማስወጣት ቢቻልም ከሰሞኑ መልሶ በመከሰቱ  በግጦሽ ቦታዎችና በለማ ሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

በተከሰተው የአንበጣ መንጋም 1 ሺህ 134 ሄክታር መሬት በመኽር የለማ ሰብል እና 18 ሺህ 800 ሄክታር የሚበልጥ የግጦሽ ቦታ መውረሩን ገልፀዋል።

የአንበጣ መንጋውም የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ በየቀኑ በማሳተፍ በባህላዊ መንገድ የመከላከል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም 10 ሺህ ሊትር ኬሚካል ቀርቦ ርጭት እየተካሄደ መሆኑን አመልክተው እስከ አሁንም በወርኢሉና ደሴ ዙሪያ ወረዳዎች 200 ሊትር በመጠቀም መርጨት መቻሉን አመልክተዋል።

አሁንም በቀሩ 8 ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ የመድሃኒት የማቅረብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰውዋል።

የአንበጣ መንጋውን በባህላዊ መንገድ መከላከል የበለጠ ውጤታማ መሆኑን አመልክተው አርሶ አደሩን በማደራጀት የሚረብሽ ድምፅ በማሰማት የመከላከል ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የአንበጣ መንጋው በፍጥነት መከላከል ካልተቻለ ሰብልን ሙሉ በሙሉ የማውደም አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ አርሶ አደሩ ማሳውን ሳይሰለች በመፈተሽ የመከላከል ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መክረዋል።

በቃሉ ወረዳ የ06 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኢብራሂም አህመድ በበኩላቸው በየጊዜው ብቅ ጥልቅ የሚለው የአንበጣ መንጋ ከምርት ውጭ ያደርገናል የሚል ስጋት አድሮብናል ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት አንድ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ማሽላና ማሾ በከፊል ያወደመባቸው መሆኑ አስታውሰው  አሁንም በመኸር አዝመራው  በዘሩት ማሽላ ላይ በመከሰቱ ቤተሰቦቻቸውን በማሳተፍ  በባህላዊ መንገድ የመከላከል ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የሚረብሽ ድምጽ በማሰማት  ከማሳቸው የማስወጣት ስራ እየሰሩ ቢሆንም መንግስት ኬሜካል በመርጨት እንዲያግዛቸውም ጠይቀዋል።

ሌላው የለጋ አምቦ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አወል ሰይድ እንደገለፁት ሰሞኑን የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ግማሽ ሄታር መሬት ላይ በዘሩት ስንዴ የተወሰነ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡

በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ በባህላዊ መንገድ እየተካላከሉ መሆናቸውን ጠቅሰው አንበጣው ከአርሶ አደሩ አቅም በላይ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ መንግስት ኬሚካል በማቅረብ ሊያግዝ ይገባል ብለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን በዚህ የመኸር ወቅት ከሚለማው 441 ሺህ ሄክታር መሬት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡