በጉጂ ዞን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች የ212ቱ ግንባታ ተጠናቀቀ

66

ነገሌ (ኢዜአ) ሐምሌ 15/2012  በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በአንድ ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች መካከል የ212ቱ ግንባታ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የዞኑ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዳዲ ኩራ በዞኑ 355 ፕሮጀክቶች 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ ግንባታቸው ተጀምሮ በሂደት ላይ እንደነበሩ አመልክተዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥም የመጠጥ ውሃ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመስኖ ፣ የጤናና የመንገድ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ በግንባታ ሂደት ላይ ከነበሩት ፕሮጀክቶች መካከል 212ቱ ሙሉ በሙሉ በመጠናቀቃቸው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል ፡፡

ከመልካም አስተዳደር ጉድለትና ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከ4 እስከ 5 ዓመታት የተጓተተ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

የፕሮጀክቶቹ ወጪ በአብዛኛው በፌደራልና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በጀት የተሸፈነ እንደሆነ ነው አቶ ዳዲ ያብራሩት፡፡

ፕሮጀክቶቹን ተዘዋውረው የጎበኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶ እንዳሉት የቀሪዎቹ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የተጠናከረ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ አሁን ግንባታቸው ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች አንድ ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም አብራርተዋል፡፡

አስተያየት የሰጡ የነገሌ ከተማ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ ሻለቃ መታ ሞሉ እንዳሉት እነዚህ ፐሮጀክቶች ለዓመታት ለዘለቁት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ናቸው፡፡

ከእነዚህ መካከል የገናሌ መጠጥ ውሃና የቦሬ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ተቋም ፕሮጀክቶች ግንባታ ለ10 ዓመታት መጓተታቸውን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

በመንግስት የተጀመሩትን አዳዲስና የተጓተቱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን የማጠናቀቅ ስራው የአንድ ወቅት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም