በህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት በዓበይት ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መደረሱ ተገለጸ

45

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2012(ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት በዓበይት ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የአፍሪካ ህብረት ዓባላት ቢሮ መሪዎች ባሳለፍነው ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ የመነጨ መፍትሔን ማበጀት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በዚህም በግድቡ የውኃ ሙሌት እና ዓመታዊ የሥራ ክንውን ላይ ያተኮረውና ካለፈው የቀጠለው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ልዩ ስብሰባ ትናንት ተካሄዷል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የሚያደርጉትን ድርድር አጀንዳው ያደረገው ስብሰባ፣ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር በሆኑት ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ አመቻችነት መካሄዱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፣የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክና የግብጽ ፕሬዚዳንት አብዱልፋታህ አል ሲሲ ተሳትፈዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃመትን ጨምሮ የቢሮው አባላት የሆኑት የኬንያ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የማሊ ሀገራት መሪዎች እና ተወካዮችም ታድመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሦስቱ ሀገራት ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዲችሉ የአፍሪካ ኅብረት ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎችን የማበጀት ሥራ አስቀድሞ በነበሩ ቀጣናዊ መፍትሔ ሰጪ አሠራሮች አማካኝነት መከናወኑንም አድንቀዋል፡፡

ግብጽ እና ሱዳንን ፈጽሞ በማይጎዳ መልኩ፣ የአባይን ውኃ ፍትሐዊነት በተሞላበት እና ለሁሉም ተደራሽ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ኢትዮጵያ ባላት ውሳኔ እንደምትጸና በአጽንኦት መናገራቸውን ነው መግለጫው ያመለከተው።

በቀጠናው የታየው ወቅታዊ የዝናብ እና የፍሰት መጠን መጨመር ግድቡን ለመሙላት ሁኔታዎችን አመቺ ማድረጉም ተገልጿል፡፡

የግድቡን የመጀመሪያ የውኃ ሙሌት እና ዓመታዊ የሥራ ክንውን አስመልክቶ፣ ኢትዮጵያ ሚዛናዊ እና ሦስቱ አገራት በፍትሐዊነት ከዓባይ ወንዝ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ድርድርን ለማካሄድ ባላት አቋም እንደምትቀጥልም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከተገኘው ከፍተኛ የዝናብ መጠን የተነሣ፣ የግድቡ የመጀመሪያ ዓመት የውኃ ሙሌት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ውኃው በግንባታ ላይ ያለውን ግድብ አልፎ እየፈሰሰ እንደሚገኝም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በሀገር መሪዎች እና ርዕሳነ መንግሥታት ደረጃ የተካሄደውን ስብሰባ፣ ሁሉም አካላት በዓበይት ጉዳዮች ላይ በመስማማት ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ድርድሩ በስምምነት እንዲቋጭ መንገድ መጥረጉ ተጠቅሷል።

በዚህም መሠረት፣ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የውኃ ሙሌቱን የተመለከቱ የቴክኒክ ውይይቶች በአፍሪካ ኅብረት በኩል በሚደረገው ሂደት እንዲቀጥሉ እና ወደ አጠቃላይ ስምምነት እንዲደረስ መስማማታቸው ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም