በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ የተከሰተውን የኩፍኝ በሽታ ለመከላከል እየተሰራ ነው

77
ጋምቤላ ሐምሌ 3/2010 በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ የተከሰተውን የኩፍኝ በሽታ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዋና የስራ ሂደት አቶ ኦኬሎ ቾል ለኢዜአ እንደገለጹት በወረዳው መኮይ ቀበሌ ከሰኔ 27 ቀን 2010 ጀምሮ የኩፍኝ በሽታ ተከስቷል፡፡ በሽታውን ለማረጋገጥ ናሙናዎች ወደ ኢትየጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዮት ተልኮ  በሽታው ስለመሆኑ የሚያሳይ ውጤት መምጣቱንም ገልጸዋል። በበሽታውም እስካሁን 40 ሰዎች የተያዙ ሲሆን የሁለት ህፃናት ህይወት ማለፉንም ተናግረዋል። “በአሁኑ ወቅትም በሽታው በተከሰተበት ቀበሌ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ቅድሚያ በመስጠት የበሽታው መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው'' ብለዋል። በሽታው በህፃናት ላይ ይባስ እንጂ ወጣቶችንም የሚያጠቃ ስለሆነ በቀጠይም ከአምስት ዓመት ጀምሮ ለሚገኙ ህፃናትና ታዳጊ ወጣቶች በተመሳሳይ መልኩ ክትባት ለመስጠት አስፈላጊው መድኃኒት እየተላከ መሆኑን ገልጸዋል። በሽታው በወረዳው በሚገኙ ቀበሌዎችና ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዳይዛመት የተቀናጀ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ በተጠናከረ መልኩ የክትትልና የቅኝት ስራዎች እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል። በሽታው ዓይን የማስለቀስ፣ በሰውነት ላይ ሽፍታ የማወጣት፣ የአፍንጫ ፈሳሽና ሌሎች ምልክቶችን ስለሚያሳይ ህብረተሰቡ የተጠቀሱት ምልከቶች የታዩበትን ህፃንም ሆነ ወጣት በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መውሰድ እንዳለባችውም አቶ ኦኬሎ አሳስበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም