በማእከላዊ ጎንደር ዞን 2 ሺህ ሄክታር መሬት በቢራ ገብስ እየለማ ነው

91
ጎንደር ሐምሌ 3/2010 የኩታ ገጠም እርሻ ጊዜና ጉልበትን በመቆጠብ ምርታማነታችን ከፍ እንዲል አግዞናል ሲሉ በቢራ ገብስ ልማት የተሰማሩ የማእከላዊ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ በዞኑ በተያዘው የመኸር ወቅት 2 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በቢራ ገብስ ዘር የተሸፈነ ሲሆን ከ3 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ደግሞ በልማቱ በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በተበጣጠሰ መንገድ የሚካሄደው የቢራ ገብስ ልማት ለእርሻ፣ ለዘር፣ ለአረምና ለምርት ስብሰባ በርካታ የሰው ጉልበትና ጊዜን የሚፈጅ በመሆኑ አድካሚ እንደነበር የገለፁት በወገራ ወረዳ በቢራ ገብስ ልማት የተሰማሩት አርሶ አደር ግስሜ ማሞ ናቸው፡፡ “እኔና አምስት ተጎራባች አርሶ አደሮች በቢራ ገብስ ልማት በጀመርነው የኩታ ገጠም የእርሻ ስራ ከሶስት አመት በፊት ከግማሽ ሄክታር አገኝ የነበረውን 10 ኩንታል ምርት አምና ወደ 12 ኩንታል ለማሳደግ አስችሎኛል'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “የኩታ ገጠም እርሻ የአርሶ አደሩን በጋራ የመስራት ባህል የሚያጎለብት ነው'' ያሉት ደግሞ በወገራ ወረዳ የኮሶዬ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አየልኝ መኳንንት ናቸው፡፡ “የኩታ ገጠም አርሻ ከጀመርኩ ሁለት አመት አልፎኛል'' የሚሉት አርሶ አደር አየልኝ በተለይ በቢራ ገብስ ልማቱ የተሰማራን አርሶ አደሮች በጋራ በማረስ ምርጥ ዘርና ማደበሪያ በመጠቀም በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ አስገኝቶልናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደር መልኬ ሲሳይ በበኩላቸው ዘንድሮ በኩታ ገጠም እርሻ ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በቢራ ገብስ መሸፈናቸውን ገልጸዋል፡፡ የግብርና ባለሙያዎች በሰጧቸው ምክር በመታገዝ በመስመር የዘሩት የቢራ ገበስ ቡቃያው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ አምና ከግማሽ ሄክታር 12 ኩንታል አግኝቻለሁ ዘንድሮ ደግሞ አዳዲስ የግብርና አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀሜ የሁለት ኩንታል ጭማሪ አገኛለሁ ብዬ እገምታለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የማእከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ አበበ አለሙ በዘንድሮ የክረምት የሰብል ልማት ሁለት ሺ ሄክታር መሬት በቢራ ገብስ እየለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ “ከ 3ሺህ በላይ አርሶአደሮች በቢራ ገብስ ልማቱ በመሳተፍ ላይ ናቸው'' ያሉት ባለሙያው በምርት ዘመኑ በቢራ ገብስ ከለማው መሬት ከ 48 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ የአርሶአደሩን ምርታማነት ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት በዞኑ በቢራ ገብስ ልማት የተሰማሩ  ከሁለት ሺህ በላይ አርሶአደሮች በኩታ ገጠም እርሻ እንዲሳተፉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ለአርሶአደሮቹ ከአንድ ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የቀረበ ሲሆን የሚያመርቱትን የቢራ ገብስ በቀጥታ ለጎንደር የቢራ ብቅል አምራች ፋብሪካ ማስረከብ እንዲችሉም በማህበራት በኩል የገበያ ትስስር እንደሚፈጠር ገልጸዋል፡፡ በጎንደር ከተማ የሚገኘው የቢራ ብቅል አምራች ፋብሪካ በየአመቱ ከ 400 ሺህ ኩንታል የቢራ ገብስ በግብአትነት የመጠቀም አቅም ቢኖረውም ከሀገር ውስጥ አምራቾች እየቀረበለት የሚገኘው ከ 200 ሺህ ኩንታል እንደማይበልጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም