መገናኛ ብዙሃን ሙያቸውን ለሀገር ልማትና ብልጽግና ሊጠቀሙበት ይገባል... ምሁራን

64

ደሴ፤ ሐምሌ 13/2012 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙሀን ሙያዊ ነፃነታቸውን ስነምግባሩን በጠበቀ አካሄድ ለሀገር ሰላም ፣ ልማትና ብልጽግና ሊጠቀሙበት እንደሚገባ በወሎ ዪኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ምሁራን ተናገሩ።

ምሁራኑ ለኢዜአ እንዳሉት በየትኛውን መንገድ መገናኛ ብዙሃን ሀዝብና ሀገርን በማስቀደም ለአንድነት፣ለሰላምና ለእድገት የመስራት ኃላፊነት አለባቸው።

በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ እንግዳወርቅ ታደሰ መገናኛ ብዙሃን ከሁለት ዓመታት በፊት  የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ማስፈጸሚያ ሆነው  መቆየታቸውን አውስተዋል።

ከሁለት ዓመት ወዲህ የተገኘው አንጻራዊ ነጻነት በርካታ ቁጥር ያላቸው የግል ሚዲያዎች ሁሉ በነጻነት እንዲሰሩ ከመደረጉ ባለፈ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሃሳብ ጭምር  ማካተት  መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሙያዊ ስነምግባር ውጭ ብሔርን ከብሔርና ኃይማኖትን ከኃይማኖት የሚያጋጩ በቀጥታ ስርጭት ጭምር በመታገዝ ማስተላለፋቸው ሊታለፍ የማይችል ጥፋት እንደሆነ ተናግረዋል።

"መገናኛ ብዙሃን የተቋቋሙትም ለህዝብ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማድረስ እንጂ ሀገር ለማፍረስ አልነበረም" ብለዋል።

ሙያው እውነተኝነት፣ ሚዛናዊነትና ታአማንነትን ተከትሎ መዘገብ  ቢሆንም  ተጨማሪ ጥፋት የሚያመጣ ከሆነ ግን መዘገቡ እንዲቀር የሚያስገደድ መርህ እንዳለው አስረድተዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ሙያዊ ስነምግባሩን ተላብሰው በገለልተኝነት ሀገርንና ህዝብን ማገልግል እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

መገናኛ ብዙሃን ሀገርን ለመገንባት እንደሚያገለግሉት ሁሉ በተቃራኒው ከሆነ ሀገርን የማፍረስ አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  በዩኒቨርሲቲው  የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር   አቶ ኢብራሂም ሰይድ ናቸው።

በዚህም መገናኛ ብዙሀን ሀገር የመገንባት ተልዕኳቸውን እንዲወጡ በመደገፍ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ስህተት  ላይ ሲወድቁም ሙያዊ ስነምግባርን በጠበቀ አካሄድ ፈጥኖ ማረም ይገባል ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በህዝብ ሀብት የተቋቋሙ መገናኛ ብዙሃን የግል ጥቅማቸውን በህዝብ ደም ለማሳከት የእርስ በርስ ግጭት በይፋ እስኪጠሩ ድረስ መጠበቅ አግባብ እንዳለሆነ ገልጸዋል።

አቶ ኢብራሂም እንዳሉት  ሰሞኑን  የታዋቂው አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ህልፈት ተከትሎ የጅምላ ጭፍጨፋ እንዲካሄድ በቀጥታ ስርጭት ሁሉ በቅብብሎሽ በማስተላለፍ በህዝብ ዘንድ ውዥንብር መፍጠር ኃላፊነት የጎደለው  ነው።

ከሙያው ውጪ በሆነ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የድምጸ ወያኔ፣ ትግራይ ቴሌቭዥን እና ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ላይ የተወሰደው እርምጃ ተገቢና ለሌሎች መገናኛ ብዙሃን ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።

እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ለጥፋት  መተባበራቸው አሳዛኝ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ከሙያው ስነምግባር ውጪ  እየተንቀሳቀሱ መጯጯኸ ሌላውን ደግሞ በማንኳሰስ የሚፈጽሙት ጥፋት ለእነሱም ሆነ ለሀገር እንደማይጠቅም  ያመለከቱት ምሁሩ፤ መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነምግባርን በመጠበቅ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ የመሆን ተልዕኳቸውን መርሳት እንደሌለባቸውም ተናግረዋል።

በየትኛውም መንገድ መገናኛ ብዙሃን ሀዝብና ሀገርን አስቀድመው ለአንድነት፣ ለሰላም ፣ ለእድገትና ለብልጽግና የመስራት ኃላፊነታቸውን በተገቢው ሊወጡ እንደሚገባም ምሁራኑ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም