የኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት ነው–ግብፅ

1536

ሃምሌ 3/2010 የኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት በግጭት ላይ ለሚገኙ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት እንደሚሆን ግብፅ ገለጸች።

ግብፅ የኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች በሁለቱ ሀገራት መካከል የቆየውን አለመግባባት በመሻር የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት በመፈራረማቸው መደሰቷን ገልጻለች።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የወዳጅነት ግንኙነት እንድትጀምር ባሳለፍነው እሁድ አስመራ ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል እንዲሁም በቀጣናው ፀጥታና መረጋጋት እንዲሰፍን ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተወያይተዋል።

ከውይይታቸው በኋላም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ጦርነት በይፋ እንዲቆምና የሰላምና ወዳጅነት አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ እንዲጀመር ሁለቱ መሪዎች ስምምነት ተፈራርመዋል።

ይህ የሁለቱ ሀገራት ስምምነት በግጭት እና አለመግባባት ውስጥ ለሚገኙ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት እንደሚሆን ነው የተገለፀው።

የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በአፍሪካ ልማት እና የጸጥታ ስራዎች ላይ ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራና ሌሎች የአህጉሪቱ ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ጠቁሟል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ እና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከተፈረመው ስምምነት ውስጥ የሁለቱን ሀገራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመርና ማደስ ይገኙበታል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከአስመራ መልስ ትናንት አዲስ አበባ ላይ በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረመውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረዋል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ባለፈው ግንቦት ወር ባካሄደው ስብሰባ የአልጀርሱን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበለው ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተሾሙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ከኤርትራ ጋር ወዳጅነት የመፍጠር እቅድ መኖሩን ይፋ ማድረጋቸውም ይታወቃል።

ምንጭ፦ዥንዋ