ዱራሜ- አንጋፋና ስመ ጥር ስፖርተኞችን ከማፍራት ባሻገር ነገንም ታስባለች

312

አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አንጋፋና ስመ ጥር ስፖርተኞችን ያፈራችው ዱራሜ ከተማ ወጣት ስፖርተኞችን ለማፍራት ተግቼ እየሰራሁ ነው ትላለች።

የዱራሜ ከተማ በስተ ደቡብ የኢትዮጵያ አቅጣጫ መገኛ የሆነው የከምባታ ጠምባሮ ዞን ርዕሰ ከተማ ናት።

ከተማ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ስመ ገናና የሆኑና ለዕድገቱ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ድንቅ እግር ኳስ ተጫዋቾችን አፍርታለች።

ከእነዚህም መካከል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ባለፉት ሁለት አሥርት አመታት ስማቸው በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ባለቤት ነች።

ከነዚህም መካከል አንዱ አዳነ ግርማ ነው።

አዳነ በሐዋሳ ከተማ እንዲሁም በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች ውስጥ ተጫውቷል።

በክለቦቹ ባሳለፈባቸው ጊዜያትም በዋንጫዎች የታጀበ ድንቅ ጊዜ አሳልፏል።


ተጫዋቹ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ለ10 ዓመታት በመጫወትም አንጋፋ ለመሆን የበቃና ከዋልያዎቹ ጋር ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞ ጉልህ አስተዋጽኦ ያደረገ ተጫዋች ነው።

የብሔራዊ ቡድኑ ምሰሶ ስለነበረም በኢትዮጵያ ስፖርት ቤተሰቦች ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይዟል።

ሌላኛዋ የዱራሜ ፈርጥ የሆነችው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ድንቅ የፊት መሥመር አጥቂ እግር ኳሰኛዋ ሎዛ አበራ ናት።

ከትውልድ ከተማዋ የተነሳው የሎዛ የእግር ኳስ ሕይወት በሐዋሳ ከተማና በደደቢት እግር ኳስ ክለቦች ድንቅ ብቃቷን አሳይታብታለች።የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ኮከብም ሆና አብርታለች።

በማልታ ቢርኪርካራ እግር ኳስ ቡድን ድረስ በመዝለቅም ግብ አምራች ተጫዋች ሆና የራሷንና የአገሯን ስም አስተዋውቃለች።

በኢትዮጵያ በርካታ ዕድሉን ያላገኙና ያልተዘመረላቸው እግር ኳስ ተጫዋቾች በከተሞችና በየሠፈሩ እንደሚገኙ አያጠራጥርም።

በደቡብ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የምትገኘው ዱራሜም ለዚህ ማሳያ ነች።

የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሠናይት ለገሠ እንደሚሉት በዞኑ ተፈጥሯዊ የስፖርት ብቃትን የተላበሱ በርካታ ታዳጊ ወጣቶች ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ በክለብ ደረጃ የአምባሪቾና ሺንሺቾ እግር ኳስ ፣ በዱራሜና በአንጋጫ ከተሞች የእጅ ኳስ ክለቦች ተቋቁመዋል።  

ዞኑ ታዳጊና ወጣት ብቁ ስፖርተኞችን ከአገር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፍ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ለማውጣትና ለማበራከት እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚወጡ ስፖርተኞች ከትውልድ ቀያቸው ባሻገር ለአገራቸውም ስፖርት ዕድገት ሚና እንዳላቸው ይታመናል።

መንግሥት ብቃት ያላቸውና  አገራቸውን የሚጠቅሙ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ለዞኑ ድጋፍ ቢያደርግ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለዋል።