በአፍሪካ የኮቪድ 19 የምርመራ አቅም እያደገ ነው

56

አዲስ አበባ  ሀምሌ 9/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በኮቪድ19  ምርመራ  ቀዳሚ ሆነች፡፡

ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኮቪድ19 ተጠቂዎችን በመርመር  ቀዳሚ ስትሆን፤ ከአፈሪካም ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሞሮኮ፣ከግብጽ እና ጋና በመቀጠል አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ሲዲሲ አፍሪካ አስታወቀ።

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል እንዳስታወቀው፤ በአፍሪካ በኮቪድ 19 የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን አልፎ 644 ሺሕ 205 የደረሰ ሲሆን በዚያው ልክ እያገገሙ ያሉ ሰዎች ቁጥርም ከሩብ ሚሊዮን አልፎ 334 ሺሕ 547 ሆኗል።

የቫይረሱ ተጠቂዎቹን ቁጥር ለመለየትና የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የመመርመር አቅምን ማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዛሬ እንዳስታወቀው፤ ከአፍሪካ 2ሚሊዮን  278 ሺሕ ሰው በመመርመር ደቡብ አፍሪካ በአንደኝነት ስትቀመጥ፤ ሞሮኮ 934 ሺሕ 48፣ ግብጽ 934 ሺሕ 87፣ ጋና 336 ሺሕ 93፣ ኢትዮጵያ 302 ሺሕ 728 ሰዎች በመመርመር ከሁለት እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ከፍተኛ ምርመራ አድርገዋል ተብለው የተጠቀሱት አምስቱ ሀገራትም  በድምሩ 342 ሚሊዮን625 ሺሕ 897 ሰዎችያሏቸው ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ 114 ሚሊዮን 963 ሺሕ 5 ሰው በመያዝ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ እንደሆነች ማዕከሉ አስታውቋል።

ከምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 14 ሀገራት ኢትዮጵያ 302 ሺሕ 728 ሰዎችን በመመርመር ቀዳሚ ናት።

ኡጋንዳ 232 ሺሕ 608፣ ኬኒያ 225 ሺሕ 495 ፣ ሩዋንዳ 194  ሺሕ 802 ሰዎች በመመርመር ከሁለት እስከ አራትኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን የማዕከሉ መረጃ ያመለክታል።

በአፍሪካ ይሄ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ 644 ሺሕ 205 ሰዎች በኮቪድ19 የተያዙ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 334ሺሕ 547ቱ አገግመው፣ 14ሺሕ 44ቱ ሞተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም