በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን ያወደሙ አካላት በአፋጣኝ ለሕግ እንዲቀርቡ ተጠየቀ

76

 አዲስ አበባ  ሀምሌ 8/2012  (ኢዜአ) ተከስቶ በነበረው ሁከትና ግርግር ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ውድመት ያደረሱ አካላት በአፋጣኝ ለሕግ እንዲቀርቡ በባሌ ዞን የአጋርፋ የአገር ሽማግሌዎች ጠየቁ፡፡ 

በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ ሕዝብ ሲገለገልባቸው የነበሩ 37 ተቋማት ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የወረዳው አስተዳደር አረጋግጧል። 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የወረዳው የአገር ሽማግሌዎች ከረጅም ዓመታት በፊት በሕዝብ ተሳትፎ ተገንብተው አገልግሎት ሲሰጡ የኖሩ የመንግስት ተቋማት በመቃጠላቸው ማዘናቸውን ገልጸዋል።

በተቋማቱ ከልጅነት እስከ ሽምግልናቸው የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲያገኙ መኖራቸውን፤ ልጆቻቸውም ተቀጥረው እንጀራ እየበሉባቸው እንደነበረ ተናግረዋል።

የአገር ሽማግሌዎቹ አቶ አደም ዳውድ እና አቶ ታደሠ ኢደኤ በክብር ሲገለገሉባቸው የነበሩት የመንግስት ተቋማት ባልታወቀ ምክንያት በአንድ ጀንበር በእሳት መውደማቸውን ተናግረዋል።

ከሰው የተፈጠረና አዕምሮ ያለው ትውልድ ይህን በማድረጉ ማዘናቸውንም ገልጸዋል።

አጥፊዎቹ ሁሉንም የመንግስት ተቋማት ከህይወታችን ጋር ከፍተኛ ቁርኝት የነበረውን የግብርና ቢሮ ጭምር አውድመውብናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ መኮ አደም ናቸው።

አሁን በሁለት ሰዎች መካከል አለመግባባት ቢፈጠር የሚዳኙበት ቦታ እንኳን አለመኖሩን ገልጸዋል።

እርሳቸውም በወደሙት ተቋማት እዛው ተወልደው ያደጉ ልጆቻቸው ይሰሩ እንደነበር ተናግረዋል።

የአገር ሽማግሌዎቹ እነኚህን የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ያቃጠሉባቸው አካላት ለሕግ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል።

አጥፊዎቹን ወደ ሕግ ለማቅረብ ተባባሪ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በወረዳው ይህ ጥፋት ከተፈጸመ በኋላ ወረዳ አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት አቶ አብዱልቃድር ኡስማን  የቀድሞ የወረዳውን አስተዳዳሪ ጨምሮ በጉዳዩ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ ሁለት የካቢኔ አባላትና ዘጠኝ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

ይህ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

ሕዝቡ የወደሙትን የመንግስት ተቋማት መልሶ ለመገንባት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ቃል መግባቱንም አቶ አብዱልቃድር ተናግረዋል።

በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ ሁከትና ግርግር በማስነሣትና የሰው ሕይወት በማጥፋት የተጠረጠሩ ከ200 መቶ በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም