በአርሲ ነጌሌ በነበረው ሁከት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች መንግስት እንዲያቋቁማቸው ጠየቁ

89

አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2012(ኢዜአ) በአርሲ ነገሌ ከተማ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ግርግር ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች መንግስት አጥፊዎችን ለሕግ እንዲያቀርብና እንዲያቋቁማቸውም ጠይቀዋል። 

ጉዳት የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች መልሶ ለማቋቋም ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን የከተማው አስተዳዳር ገልጿል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው እነዚህ ተጎጂዎች እንደገለጹት ተከስቶ በነበረው ግርግር ከልጅነት እስከ እውቀት ለፍተው ያፈሩት  ሃብትና ንብረት  በአንድ  ጀንበር ወድሞባቸዋል።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ለመቃወም  በሚል የወጡ  ወጣቶች  ንብረት ወደ ማውደም መሸጋገራቸውንም ገልጸዋል።

በሀዘንም ሆነ በደስታ ለረጅም ዓመታት ከአካባቢው ሕዝብ ጋር መኖራቸ ውን የገለጹት ተጎጂዎች ንብረታቸው በምን ምክንያት እንደወደመባቸው እንደማያውቁም ነው የተናገሩት።

አርሲ ነገሌ ከተማ "ተወልጄ አድጌያለሁ" የሚሉት አቶ ደበበ ጀማነህ ለእርሻ ግብዓትነት የሚውሉ ኬሚካሎችን የያዘው ሱቃቸው ሙሉ በሙሉ እንደወደመባቸው ነው የገለጹት።

በግርግሩ ለአርሶ አደሮች ሊያከፋፍሉት የነበረ መጋዘን ሙሉ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ የእሳት ሲሳይ እንደሆነባቸውም ተናግረዋል።

ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ያላቸውን ሃብት አውጥተውና ከወገኖቻቸው  ተበድረው የገዙት የእርሻ ግብዓት  እንደወደመባቸውም አክለዋል።

በአምቦ ከተማ ተወልደው በ12 ዓመታቸው ወደ አርሲ ነገሌ በመምጣት ኑሯቸውን መመስረታቸውን የሚገልጹት አቶ ተስፋዬ ሲሳይም ከዝቅተኛ  ደረጃ ተነስተው ያፈሩት ሃብት በአጥፊዎች መና ቀርቷል።

አቶ ተስፋዬ በልጅነታቸው ሽንኩርት በመቸርቸርና ሸንኮራ በመሸጥ መነሻቸውን መያዛቸውንና አሁን ከራሳቸው  አልፈው ለሌሎችም  ይተርፉ  እንደ ነበር ገልጸዋል።

ሆኖም የአርቲስት ሃጫሉን ሞት ለመቃወም ወጣን በሚሉ አጥፊዎች ለ40 ዓመታት ያፈሩት ሃብታቸው በአንድ ቀን መውደሙን ተናግረዋል።

ለከተማው በሰራነው መልካም ተግባር መመስገን እንጂ እንዲህ ዓይነት ውድመት ሊደርስብን አይገባም ነበር ሲሉም አቶ ደበበ ጨምረው ገልጸዋል።

የወደመባቸውን ንብረት ተክተው ወደ ስራ ለመመለስ አቅም እንደሌላቸው በመግለጽም መንግስትና የአካባቢው  ማኅበረሰብ  እንዲያቋቁማቸው  ጠይቀዋል።

የአርሲ ነገሌ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ አቶ አሊዩ ዋታ በተፈጠረው ሁከትና ግርግር የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ዘጠኝ ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸውን ገልጸዋል።

መኖሪያና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በርካታ ሕንፃዎችና ተሸከርካሪዎች መቃጠላቸውንም ተናግረዋል።

የወደመውን ንብረት ወደ ነበረበት ለመመለስ ከአካባቢው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ  ክልል  የተለያዩ  አካባቢዎች በተከሰተ ሁከት ንብረታቸው የወደመባቸውን ዜጎች የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ መልሶ እንደሚያቋቁም የክልሉ መንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ባለፈው ሳምንት መግለጻቸው ይታወቃል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም