የምከር ቤቱ አባላት በጋምቤላ ክልል የኮሮና ወርሽኝን ለመግታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳሰቡ

59

ጋምቤላ (ኢዜአ) ሐምሌ 8/2012) በጋምቤላ ክልል እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ወርሽኝ ለመግታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ።

የምክር ቤቱ  ቋሚ ኮሚቴዎች በኮሮና ወረርሽኝ መከላከል፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት  የልማትና መልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ትናንተ በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።


የኮሚቴዎቹ አባላት በዚህ ወቅት  ቫይረሱን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ  አዋጅ ድንጋጌዎችን  በአግባቡ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምሮ የተጠናከረ የመቆጣጠር ስራዎች ሊከናወኑ እንደሚገባ አመልክተዋል።


ከአባላቱ መካከል  አቶ ኡሞድ ተፋላ እንዳሉት በክልሉ እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ወረርሽኝ  መግታት ካልተቻለ የከፋ ቀውስ ሊያደርስ ይችላል።


ወረርሽኙን ለመከላከል  የአዋጁ ድንጋጌዎች በአግባቡ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምሮ በየዘርፉ ባሉ አደረጃጀቶች የተጠናከሩ ስራዎች ሊከናወኑ ይገባል ብለዋል።

የኮሮና ወረርሽን ህክምና የመደበኛው የህክምና አገልግሎት በማይጎዳ መልኩ መከናወን እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ  ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ወይናቶ አበራ ናቸው።


በተለይም በመደበኛ ታካሚዎች ስጋት እንዳይፈጠር  የኮሮና ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መቀራረብ እንደሌለባቸውም ጠቁመዋል።


የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በሰጡት ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት መጠን ከቀን ወደ ቀን እየጨመሩ  መምጣቱን ገልጸዋል።


የኮሮና ወረርሽኝን የመከላከሉ ስራ ለግብረ ኃይሉ ብቻ የመተው አዝማሚያዎችን በማስቀረት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሁሉም አመራር ሊረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።


"በተለይም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ለማስገባት ትልቅ ፈተና እየሆነ ነው " ያሉት ደግሞ  የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊና የኮሮና መከላከል የቴክኒክ ኮሚቴ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ካን ጋልዋክ ናቸው።


ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያና የህክምና ማዕከል ያለመግባታቸው ደግሞ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት የችግሩን አሳሰቢነት በመገንዘብ ወረርሽኙን ለመግታት የተቀናጀ ርብርብ ለማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።

በውይይት መድረኩ  የማህበራዊ ፣ መሰረተ ልማት ፣ በጀትና ፋይናንስ ፣ ህግና ፍትህ ፣ ኢኮኖሚ፣ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም