ስልጣን በአቋረጭ ለመያዝ የሚደረገው ጥረት የሀገርን አንድነት እንደሚጎዳ ምሁራን ተናገሩ

71

ሆሳዕና (ኢዜአ)  ሐምሌ 7/2012 ለግል ጥቅም ህዝቦችን  በመለያየት  ስልጣንን በአቋራጭ ለመያዝ የሚደገረው ጥረት የሀገርን አንድነት የሚጎዳ በመሆኑ  ሊታረም እንደሚገባ   የዋቸሞ ዩንቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ምሁራን እንዳሉት ህብረተሰቡን በማሳሳት  ለዘመናት ተቻችሎ የኖረውን ውህደት ለማፍረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተገቢነት የለውም።

በዩኒቨርሲቲው  የሶሻል አንትሮፖሎጂ  ምሁር  ዶክተር ወርቁ ያዕቆብ በሰጡት አስተያየት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ለማከናወን ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ሂደቱን ለማስተጓጎል የተቀነባበረው ሴራ የሚያሳዝን ነው።

መንግስት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ባይቆጣጠረው       ሀገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ ሊያስገባት ይችል ነበር ብለዋል"

ብሔርን ከብሔር ፣ ኃይማኖትን ከኃይማኖት ለማጋጨት  የሚሞክሩት ለግል ጥቅማቸው ስልጣን በአቋራጭ ለመያዝ የሚታትሩ አካላት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የፖለቲካ ርዕዮተ አለም የሚባለው ህዝብን ከድህነትና ኋላ ቀርነት  በማምጣት ለስኬት የሚያበቃን ሀሳብ አፍልቆ የፖለቲካ ትግል ማድረግ እንጂ ዜጎችን በስሜት በመቀስቀስ ያልተገባ ሂደት ውስጥ ማስገባት

የተሳሳተ አካሄድ ነው ብለዋል፡፡ 

በዚህ ረገድ የሚደረገውን ማንኛውምንም እንቅስቃሴ በንቃት መከታተልና ማረም  እንደሚገባ ያመለከቱት ዶክተር ወርቁ በተሳሳተ መንገድ ከመመራት ይልቅ ለቤተሰቡና ሀገር የሚጠቅመውን መለየት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

መገናኛ ብዙሀን ፣  ሲቪክ  ማህበራትና ኃይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸውን መልካሙን በማሳየት  የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ የጥፋት ኃይሎችን ለህግ አሳልፎ መስጠትና  መንግስትም ስርዓት ማሲያዝ  እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው  የግብርና ኮሌጅ ምሁር   ዶክተር ደምበሎ ቲሌ በበኩላቸው በሀገሪቱ በዚህን ወቅት የተቃጣው ጥቃት የኢትዮጵዊያንን አብሮነት ለመናድና የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማደናቀፍ የታቀደ ተግባር እንደነበር  ገልጸዋል።

በተወዳጁን አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴንሳ ላይ የተፈጸመው ጥቃት  ተቻችሎ የኖረውን ህዝብ ሰላም ለማደፍረስና የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል የተደረገ ሙከራ ነው ብለዋል፡፡

መሰል አስነዋሪ ተግባር በማከናወን ስልጣን መያዝም ሆነ ሀገር መምራት እንደማይቻል ጠቁመው በዚህ ወቅት ተወዳዳሪ ሃሳብ በማቅረብ ያለ ግጭት የስልጣን ባለቤት መሆኑን እንደሚቻል በህገ መንግስቱ እንደተደነገገ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም