ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ መተካት የሚያስችል ትስስር ተፈጠረ

63

አዲስ አበባ፤ ሀምሌ 7/2012 (ኢዜአ) ንግድና ኢንዱስትሪ እና የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴሮች ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በአገር ውሰጥ መተካት የሚያስችላቸውን የትስስር ዕቅድ ይፋ አደረጉ። 


ኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚሆን ግብዓት ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወጪ ታደርጋለች።

ለአብነት ለብረትና ብረት ነክ ግብዓቶች 850 ሚሊዮን ዶላር፣ ለኬሚካልና ኮንስትራክሽን ደግሞ ከ950 ሚሊዮን ዶላር በላይ በዓመት ወጪ እንደምታደርግ መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህን መነሻ በማድረግ ሁለቱ ተቋማት በአገር ውስጥ የሚመረቱ ማዕድናትን በግብዓትነት ለሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ ትስስር ፈጥረዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አምራች ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ እንዳይሆን ከሚያደርጉ ችግሮች አንዱ የግብዓት እጥረት መሆኑን ይገልጻሉ።

ከውጭ የሚገቡ የምርት ግብዓቶች አገሪቷን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ ከመዳረጋቸው ባለፈ ተወዳዳሪነታቸውን በዘላቂነት ሊያሳድግ እንደማይችልም ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ከማዕድን ዘርፉ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ወጪን በማስቀረት የኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ይረዳል።

በግንባታው ዘርፍ ብቻ እስከ 70 በመቶ የግንባታ ግብዓት ከውጭ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ይህንን በአገር ውስጥ መተካት ካልተቻለ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪ ማድረግ እንደማይቻል ተናግረዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በ2013 ዓ.ም የማርብልና ግራናይት ምርቶችን ሙሉ ለሙሉ በአገር ውሰጥ ለመተካት ማቀዱንም ሚኒስትሩ አቶ መላኩ ጠቁመዋል።

የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰልን ሙሉ ለሙሉ መጠቀም በጀመሩ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዓመት ይወጣ የነበረውን 220 ሚሊዮን ዶላር ማስቀረት መቻሉንም ገልጸዋል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኩዋንግ ቱትላም በበኩላቸው ቅንጅታዊ አሰራሩ በተለያየ ምክንያት ሥራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ሥራ ለማስጀመር ያግዛል ብለዋል።

ክምችታቸው በጥናት የተረጋገጠና ወደ ምጣኔ ሃብት ጠቀሜታ ያልተቀየሩ ማዕድናትን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚረዳም ተገልጿል።

የሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ትስስር ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያችልም ነው የተነገረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም