ኢትዮጵያውያን አንድነታችን በማጠናከር የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ማጠናቀቅ ይጠበቅብናል

39

አዲስ አበባ፤ ሀምሌ 7/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን በማጠናከር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን በጋራ መቆም ያለበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሚቶ ተናገሩ።

ለትውልዱ የአገር ፍቅር ፣አንድነትና መቻቻልን ማሳወቅና ማስተማር ይገባልም ብለዋል።
በኢትዮጵያ በሕዝቦች መካከል መከፋፈልና መለያየትን የሚሰብኩ ተግባራት ይስተዋላሉ።

ውድ የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ማጥፋት፣ ለዓመታት የተደከመባቸውና በርካታ ሃብት የፈሰሰባቸውን ንብረት ማውደምን የመሳሰሉት ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ሲፈጸሙም ይታያል።

ድርጊቶቹ ሰዋዊ አስተሳሰብ በማጣት ከምክንያታዊነት ይልቅ በስሜታዊነት ተገፋፍቶ እንደሚፈጸም ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ይናገራሉ።

ይህም ሕጻናትን ከሥረ መሠረታቸው ጀምሮ የአገር ፍቅር፤ አንድነት፣ መቻቻልና መተሳሰብ ማስተማርና ያለማሳወቅ ውጤት መሆኑንም ያብራራሉ።  

የአገርን አንድነትና ሰላምን ለማምጣት ሕፃናት አገራቸውና ታሪካቸውን አውቀው ጥላቻንና መከፋፈልን ብሎም መለያየትን እያስወገዱ ማደግ ይገባቸዋል ይላሉ።

ትውልዱ ጥላቻን እንዳይማርና መጀመሪያ ሰው መሆኑን ብቻ እንዲያውቅ አድርጎ ማነጽ ይገባል ሲሉም አቶ ኦባንግ ይመክራሉ። 

ኢ-ሰብአዊነት በጎደለው መልኩ የሰውን ልጅ ሕይወት ማጥፋት፣ የአካል ጉዳት ማድረስ እንዲሁም ንብረት ማውደም ተገቢነት እንደሌለውም አመልክተዋል።

በመሆኑም ሕዝቡ በብሔር ስም የሚነግዱ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

በዚህም በተለይ ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ትውልዱ መጀመሪያ የሰውን ልጅ ክብር እንዲረዳና መልካም ስብዕናን እንዲያዳብር መሥራት አለበትም ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው በአንድነት ስሜት ግንባታውን እንዲያጠናቅቅ ጠይቀዋል።

የውጭ አለመግባባቶችና ከሁከትና ብጥብጥ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ችግሮች ለውጭ ጠላት የሚመችና ክፍተት ሳይፈጥር  በኢትዮጵያዊነት ስሜት በመነሳሳት የግድቡ ግንባታ ዳር እንዲያደርስ አሳስበዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የግድቡ ግንባታ 74 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ አሁን ላይም ግድቡ ውሃ መያዝ የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

በተያዘው ወርም 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ መያዝ ይጀምራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም