የውስጥ ልዩነቶችን በሰለጠነ አካሄድ በመፍታት እንደ አገር የተደቀኑ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ ይገባል - ኢዜማ

77

አዲስ አበባ፤ ሀምሌ 7/2012 (ኢዜአ) የውስጥ ልዩነቶችን በሰለጠነ አካሄድ በመፍታት እንደ አገር የተደቀኑ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ገለጸ።


ፓርቲው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትናንት መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የፓርቲው የሕገ ደንብ ትርጉምና የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሩሃማ ታፈሰ በአገሪቷ በተደጋጋሚ ፖለቲካዊ ሽፋን እየተሰጣቸው ከተነሱ ረብሻዎች ጋር በተያያዘ የበርካታ ንፁሃን ዜጎች ሕይወት በከንቱ ሲቀጠፍና ንብረት ሲወድም እየተመለከትን ነው ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የአገር አንድነትን የሚፈታተኑ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ወይዘሮ ሩሃማ ነገር ግን ዜጎች ሠላም የማስፈን ሃላፊነታቸው ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

መንግሥትም ረብሻዎች እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱም የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ እንዳያደርሱ መቆጣጠርና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።

እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት ለዘላቂ አገራዊ መረጋጋት መሠረት መሆኑን ፓርቲው እንደሚያምንም ገልጸዋል። 

በዚህ ጊዜ 'እንደ ተፎካካሪ ድርጅቶችም ሆነ እንደ ዜጎች ያለብን ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማወቅና በተግባር ለማሳየት መዘጋጀት ይጠበቅብናል ብለዋል። 


ከሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያዊያን በእዚህ አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳይ ከምንግዜውም በላይ በጋራ የሚቆሙበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

የውስጥ ልዩነቶቻችንን በሠለጠነ ፖለቲካ አስታርቀን እንደ አገር የተደቀኑ ተደራራቢ ፈተናችዎች በፅናት ማለፍ ካልቻልን ለትውልድ የምትሆን አገር ማሻገር እንደሚያዳግትም አመላክተዋል።

ዜጎች ይህን ፈታኝ ጊዜ በትዕግስት፣ በማስተዋልና በጥንቃቄ እንዲሻገሩትና የአገር አንድነትና ሠላም በማስጠበቅ ረገድ ሁሉም ዜጋ ግዴታውን መወጣት አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

የሕግ የበላይነትን በማክበር፣ በወንድማማችና እህትማማችነት በመተባበር በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ካለንበት ውስብስብ ችግር ወጥተን አገሪቷን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማሻገር ይገባል ነው ያሉት።

ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ዘመናዊ፣ የሰለጠነ ፖለቲካና ሕግን ያከበረ አካሄድ መከተል እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም