በአፋር ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

65
ሰመራ ግንቦት 3/2010 በአፋር ክልል የሚገኙ ግብር ከፋዮች ግዴታቸውን አውቀው ግብርን በወቅቱ በመክፈል ረገድ መሻሻል እያሳዩ መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ ኤጀንሲው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የእቅዱን 90 ነጥብ 4 በመቶ ማከናወኑን አስታውቋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሻሽሎ በወጣው  የታክስ አስተዳደርና የገቢ ግብር አዋጅ ዙሪያ በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ በኤጄንሲው የግብር አወሳሰን፣ አሰባሰብና ክትትል የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ማሄ አሊ እንደተናገሩት በክልሉ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ ይታይ የነበረው ግብርን በአግባቡ ያለመክፈል ችግር ዘንድሮ መሻሻል አሳይቷል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተለያየ የገቢ ርእስ ለመሰብሰብ ከታቀደው 570 ሚሊዮን ብር ውስጥ ከ507 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡ የተሰበሰው ገቢ ከእቅዱ 90 ነጥብ 4 በመቶ የተከናወነ ሲሆን ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ150 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ ብልጫ ሊያሳይ የቻለውም በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ የመሰብሰብ አቅም መጨመርና የንግዱ ህብረተሰብ የመንግስትን ግብር በአግባቡና ወቅቱን ጠብቆ የመክፈል ሁኔታ መሻሻል እያሳየ በመምጣቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዘርፉ የሚስተዋለው ኪራይ ሰብሳቢነትና ገቢን የመሰወር ችግር ለመፍታት ኤጀንሲው በየደረጃው ከሚገኙ የፍትህ አካላት ጋር  በቅንጂት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አሊሚራህ አብዴላ  በግብር አከፋፈል ዙሪያ የሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ድርጊትን ለመቆጣጠርና የንግዱ ህብረተሰብም  ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ለማድረግ ከኤጄንሲው ጋር ተቀራርበው በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ የቡሪሙዳይቶ ወረዳ ዳኛ  አቶ አደም ኢጎ በሰጡት አስተያየት መንግሰት የንግድ ስርአቱን  ለማዘመን የሚያወጣቸው የህግና የአሰራር ማሻሻያዎች ተግባራዊ እንዲሆኑና በዘርፉ የሚስተዋሉ ህገወጥ ድርጊቶች እንዲታረሙ በአካባቢያቸው ህብረተሰቡን በማስተማርና ህጎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስረድተዋል፡፡ በሰመራ ከተማ ትናንት በተጀመረውና ለአምስት ቀናት በሚካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ከአምስት ዞኖችና ከ32 ወረዳዎች የተውጣጡ ዳኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም