ለአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ በአዳማ ከ500 ሺህ በላይ ችግኝ ተተከለ

98

አዳማ ኢዜአ ሐምሌ 6/2012 በአዳማ ከተማ ለአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ ትላንት ከ500 ሺህ በላይ ችግኝ ተተከለ ።
በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንደገለፁት የኦሮሞ ህዝብ ወደ ባህሉና ስነ ልቦናው ተመልሶ "ማፍረስ ሳይሆን ማልማትና መገንባት እንደሚቻል ያሳየበት ቀን ነው" ብለዋል ።
 
ህዝቡ ለታጋዩና የሰብአዊ መብት ተማጓቹ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያነት በመቶ ሺህዎች ሆኖ በመውጣት የችግኝ ተከላ ማካሔዱ "ለጠላቶች የመጨረሻው ውድቀታቸው ማሳያ" መሆኑንም ተናግረዋል።
  
የህዝብ ትግል ማፍረስና ማውደም ሳይሆን ማልማት ፣ መገንባትና መትከል መሆኑን ለማሳየት ጭምር የተካሔደ መሆኑን የገለፁት ወይዘሮ ጫልቱ ህዝቡ ከልማት ጀምሮ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ አሳስበዋል ።
 
ያለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቷ በዚህ ዘመን ቁጭ ብሎ መነጋገር፣ መወያየትና በሃሳብ የበላይነት ማመንና ማሸነፍ እየተቻለ ሃሳብ የሌላቸው በጉልበት የሚያምኑ ሰዎች ህዝቡን እያነሳሱ ለጥፋት ዓላማ የማሰማራት አማራጫቸው የከሸፈባቸው መሆኑንም ተናግረዋል ።
 
ህዝብ በእምነትና በብሔር ለማጋጨት የሚደረገውን ጥሪ ወደ ጎን በመተው የአዳማ ከተማ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ችግኝ በመትከልና በማልማት አንድነቱን ያረጋገጠበት እለት መሆኑን አስረድተዋል።
 
የሃጫሉ ዓላማ መንገድ መዝጋትና ማቃጠል ሳይሆን ህዝቦች በአንድነት ፣ በፍቅርና በነፃነት እንዲኖሩ የታገለ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኦሮሚያ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙና አህመድ ናቸው ።
 
ለሃጫሉ መታሰቢያ በክልሉ በቀጣይ 5 ቀናት ውስጥ 50 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በአዳማ ከተማ ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ የተከለው ችግኝ ለሃጫሉ መታሰቢያ ፓርክ እንዲሆን የታሰበ በመሆኑ ህዝቡ የተከለውን ችግኝ በመኮትኮትና በመንከባከብ ማሳደግ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
 
በከተማዋ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ3 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው ናቸው ።
 
በትላንትው እለት በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ ፓርክ የተለያዩ በርካታ ዛፎች መተከሉንም ገልፀዋል።
 በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ ከከተማዋ የተለያዩ ቀበሌዎች የተወጣጡ ከ70 ሺህ በላይ ወጣቶች፣ የከተማ ነዋሪዎች ፣ አባ ገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳታፊ ሆነዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም