ለችግር ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደረገው ድጋፍ የሁሉንም ተሳትፎ ይፈልጋል…አቶ ተመስገን ጥሩነህ

168

ባህርዳር ሰኔ 22/2012 በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለከፋ ችግር የተዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመታደግ ባለሀብቱና ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ገለጹ።

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ አንድ ሺህ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የዱቄትና የዘይት ድጋፍ ዛሬ ማምሻውን ተደርጓል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በድጋፍ አሰጣጥ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የኮሮ ቫይረስ ወደ ክልሉ ከገባ ጀምሮ በህብረተሰቡ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዳይደርስ ጥረት ተደርጓል።

“ለዚህም የክልሉ መንግስት ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ላይ ወጭ በማድረግ 500 ኩንታል ዱቄትና አራት ሺህ 250 ሊትር ዘይት ዛሬ ድጋፍ ማድረጉ ማሳያ ነው” ብለዋል።

በድጋፉም በኮሮና ምክንያት ለችግር የተጋለጡ አንድ ሺህ ሰዎች ለእያንዳንዳንዳቸው 50 ኪሎ ግራም ዱቄትና አራት ሊትር ዘይት እንዲደርሳቸው መደረጉን ተናግረዋል።

“እስከ አሁን በተደረገው እንቅስቃሴ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለጉዳት ለተዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ድጋፎችን የማድረግ ዝንባሌው የሚበረታታ ቢሆንም አሁን ላይ እየተቀዛቀዘ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል”ብለዋል።

የክልሉ መንግስት በባህርዳር ዛሬ የጀመረው ድጋፍ በቀጣይ በጎንደር እና ደሴ ከተሞችም የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው ባለሀብቱና ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀወጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ትኩረት የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዘላለም ልጃለም በበኩላቸው እንደገለጹት የተደረገው ድጋፍ የተቸገሩ ወገኖችን ለመድረስና ባለሃብቱን ለቀጣይ ድጋፍ ለማነሳሳት ያለመ ነው።

ይህ የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት መንግስታዊ የልማት ድርጅቶች፣ ባለሃብቶችና መንግስታት የህዝብ ወገንተኛነታቸውን በማሳየት የሚፈተኑበት መሆኑን አመልክተዋል።

“መንግስት የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው” ያሉት የድጋፉ ተጠቃሚ ወይዘሮ ስለናት መለሰ ወረርሽኙ የሚቆይ ከሆነ ችግሩ ከዚህም የከፋ ሊሆን ስለሚችል ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በወረርሽኙ ምክንያት እንቅስቃሴዎች ስለተገደቡ በተለይ ለአካል ጉዳተኞች የከፋ ችግር ይዞ እንደመጣ የገለጸው ደግሞ የዊልቸር ተጠቃሚው ወጣት ታዘበው ምህረት ነው።

የክልሉ መንግስት ዛሬ ያደረገው ድጋፍ ለአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካሞች የተሰጠውን ትኩረት የሚያመላክት በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።

የክልሉ መንግስት ከዚህ በፊትም 12 ሺህ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።