በአማራ ክልል የኮሮና ስርጭትን ለመግታት "አንቲ ቦዲ" ምርመራ ሊካሄድ ነው

60

ባህርዳር ሰኔ 22/2012 በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሰውነት በሽታ መከላከል "አንቲ ቦዲ" አቅምን ለማወቅ የሚያስችል ምርመራ ከነገ ጀምሮ በባህርዳርና ደሴ ከተሞች እንደሚካሄድ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ፀሐፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት  ጀምሮ የተለያዩ የመከላከያ እርምጃዎች ተወስዷል።

እስካሁን የቫይረሱ መከላከያ መንገዶችን በማስተማር፣ የለይቶ ማቆያና ምርመራ ማዕከላትን በማቋቋም እንዲሁም የቁሳቁስ ድጋፍ በማሰባሰብ  አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በዚህም በሰባት የላቦራቶሪ ምርመራ ማዕከላት  ከ15ሺህ የሚጠጉ  ሰዎችን በመመርመር  313  ቫይረሱ  እንደተገኘባቸውና ሁለት ደግሞ ህይወታቸው ማለፉን አመልክተዋል። 99 ሰዎች ደግሞ ማገገም ችለዋል።

ቫይረሱ አለም አቀፍ ክስተት ቢሆነም በተከናወነው ጠንካራ ስራ  የበሽታው ስርጭት ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን መደላድል መፈጠሩን አስረድተዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት  እስካሁን ሲሰራ ከነበረው በተለየ መልኩ አሁን ላይ የዳሰሳና ቅኝት ጥናት በተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በማተኮር ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ዶክተር መልካሙ የዳሰሳና ቅኝት ጥናቱን ለማካሄድም በሽታውን ለመከላከል ሰውነታችን የሚያመርታቸውን የበሽታ ተከላካይ "አንቲ ቦዲ" ላይ ያተኮረ ምርመራ በባህርዳርና ደሴ ከተሞች  በበጎ ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ  ከነገ ጀምሮ ይቀጥላል። የምርመራ ስራ ለሶስት ሳምንታት ያህል  ይቆያል።

የሰውነታችን በሽታ መከላከል አቅምም በእድሜ፣ አመጋገብ፣ በምንወስዳቸው መድኃኒቶች፣ በበሽታው ክብደትና ተጓዳኝ በሽታዎች የሚወሰን በመሆኑ በ "አንቲ ቦዲ" ውጤት ተመስርቶ ውጤታማ ህክምና ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በተጨማሪም  ማህበረሰቡ ኮሮና ምን ያህል እንደተሰራጨ በማወቅ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትና በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት ግብዓት ለማሰባሰብ እንደሚያስችል ዶክተር መልካሙ ተናግረዋል።

ምርመራውን በተሳካ ሁኔ ለማጠናቀቅም አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን በማቅረብ፣ ሙያተኞችን በመመደብና ሌሎች የቅድመ ትግበራ ሰራዎች መከናወናቸውንም አስታውቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ 6981 ነጻ የስልክ መስመርንና 0582221714 መደበኛ የስልክ ቁጥርን በመጠቀም አስፈላጊውን መረጃ ከጤናቢሮው ማግኘትና ለቢሮው ማቅረብ እንደሚቻልም አስታውቀዋል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ምርመራውን ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ህብረተሰቡና የጸጥታ ኃይሉ የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉም መልዕክታቸውን አስላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም