በደቡብ ክልል ዘላቂ ሠላምን ለመገንባት የጸጥታ መዋቅሩ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ የሠላምና ጸጥታ ቢሮ አሳሰበ

54

ሀዋሳ፣ ሰኔ 22/2012 ( ኢዜአ) በደቡብ ክልል ዘላቂ ሠላምን ለመገንባት የጸጥታ መዋቅሩ ከማንኛውም ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ አሳሳቡ።

የክልል፣ ዞንና ልዩ ወረዳዎችና የልዩ ኃይል ብርጌድ ሻለቃ አመራሮች በወቅታዊ የህግ ማስከበር ሰራዎችና በበጀት ዓመቱ የስራ አፈጻጸም ዙሪያ በሀዋሳ ከተማ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት የቢሮው ኃላፊ አለማየሁ ባውዲ እንደገለጹት በክልሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

በተለይ ተግባሩን በተፈለገው ለመምራት የጸጥታ መዋቅሩ ቁመናውና ሰብዕናው በሚፈቅደው መልኩ ለመገንባት መንግስት በወሰደው የሪፎርም እርምጃ ውጤት ቢገኝም አሁንም ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል።

በክልሉ ተለዋዋጭና ውስብስብ የሆኑ ወቅታዊ የጸጥታ ችግሮች ለመፍታት መስዋዕትነት ተከፍሎ ለውጥ ቢመጣም አሁን ላይ ስሜት ተጨምሮበት ያለው ክፍተት ለማስተካከል በተረጋጋ መንፈስ ህገ-መንግስታዊ ሃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል ብለዋል።

በየአከባቢው እየተነሱ ያሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያላቸው በመሆኑ መንግስት ተቀብሎ ህጋዊ፣ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውሰዋል።

ይህንን ሂደት ተከትሎ የህዝብን ደህንነትና ሠላም ለማስጠበቅ የጸጥታው ኃይል ህዝብን በማስተባበር በቅንጅት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

መንግስት በጀመረው ሠላማዊ ሂደት ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ባለበት ሁኔታ በተለያዩ አከባቢዎች ክልሉ እንደፈረሰ ተደርጎ እየተናፈሱና እየተፈጸሙ ያሉ ህገ-ወጥ እንቅቃሴዎች ሊታረሙ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ነቢዩ ኢሳያስ በበኩላቸው በየአካባቢው ከአደረጃጀት ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች መንግስት የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን ገልጸው በህጋዊ ሂደት ብቻ ምላሽ እንዲያገኙ ህዝብና የጸጥታ አካላት በተቀናጀ መልኩ ህግ ማስከበር ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ብለዋል።

ህጋዊ ሂደትን ያልተከተሉና ለህዝብ ደህንነት ስጋት የሆኑ እንቅቃሴዎች በመለየት ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ የጸጥታ ኃይሉ እንዲከላከል አቋም መያዙንም አስታውቀዋል።

መዋቅሩ በወንጀል መከላከል አሠራር በውስጥም ሆነ በውጭ የደረጀና የጠነከረ የሰው ኃይል ለማፍራት የክልሉ መንግስት በቂ ሃብት መድቦ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአካባቢያቸው የመዋቅር ጥያቄ መነሻ አድርጎ በጥቂት ግለሰቦች አነሳሽነት ለጸጥታ ስራ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የቤንቺ ሸኮ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ምናሉ ታደሰ ናቸው።

ሆኖም የሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና ፖሊስ ኃይሎች ባደረጉት ቅንጅት በአከባቢው ለውጥ መምጣቱንና ወደቀደመው ሰላም መመለሱን ገለጸው ከሁሉ በላይ የአከባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል።

የማህበረሰብ ተሳትፎውንና ቅንጅቱን አጠናክረው በመቀጠል ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ እንሠራለን ብለዋል።

የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ላቀው አዲሱ በአካባቢው ከማንነት ጥያቄ ጋር የተነሱ ጥያቄዎች የጸጥታ ሥራን ፈታኝ አድርገው ቢያሳልፉም ህዝብና የጸጥታ ኃይሉ በመመካከሩ እየተፈታ መሆኑን አስረድተዋል።

በአካባቢው ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ከአጎራባች ዞኖችና ህዝቦች ጋር ምክክሮች ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል።

የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ ብርጌድ አመራር ኮማንደር ኦሊ አባመጫ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይል ከማህበረሰቡ ጋር የተቀናጀ ስራ በማከናወኑ አንጻራዊ ሠላም መገኘቱን ገልጸዋል።

በአንዳንድ ችግር በተፈጠሩባቸው አከባቢዎች የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር ቢኖርም ሠራዊቱ በእግር እየተጓዘ መስዋዕት በመክፈል እየሰራ ባለበት ሂደት ህዝቡን ከጎኑ ሆኖ ጉዳቶችን ማስቀረት መቻላቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን ህዝቡ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ኮማንደር ኦሊ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም