በአማራ ክልል በድጎማ እየቀረበ ያለው የዳቦ ዱቄት ለታለመለት ዓላማ እየዋለ አለመሆኑ ተረጋገጠ

898

ባህርዳር፣  ሰኔ 22/2012(ኢዜአ) መንግስት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በድጎማ የሚያቀርበው የዳቦ ዱቄት ለታለመለት ዓላማ እየዋለ እንዳልሆነ በዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የዳሰሳ ጥናቱን  ያካሄዱት ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከአማራ ክልል ዳቦ አምራቾች ማህበር ጋር ሲሆን ፤ ከዳቦ ዱቄት ስርጭትና ከህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ በተካሄደው በዚሁ ጥናት ግኝት ዙሪያ  ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ የጥናቱን ግኝት አስመልክተው እንደገለጹት፤ መንግስት ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ በውጭ ምንዛሬ ስንዴ እያስገባ ለዱቄት ፋብሪካዎች ያቀርባል።

በድጎማ  ለአንድ ወር ከሚቀርበው 53 ሺህ ኩንታል ዱቄት ውስጥ ከ31 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው ትስስር ለተፈጠረላቸው ሁለት ሺህ 700 ዳቦ ቤቶች እንደሆነ ጠቁመው  ቀሪው ለመንግስት ሰራተኞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች እንደሚሰራጭ አመልክተዋል።

ለዳቦ ቤቶች የሚቀርበው ዱቄትም በተቀመጠለት ልኬታ መጠን ዳቦ ተመርቶ  ለህብረተሰቡ መቅረብ ሲገባው አብዛኛው ዱቄት በጥቁር ገበያ አየር በአየር የሚሸጥ መሆኑን በጥናቱ ተረጋግጧል ብለዋል።

በተጨማሪም ከአንዳንድ የንግዱ ማህበረተሰብ ስነምግባር መጓደል ጋር ተያይዞ ተጋግሮ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ የሚቀርበው የዳቦ መጠን በትክክል እየቀረበ እንዳልሆነም  እንዲሁ።

በየደረጃው ባለው መዋቅር ችግሩን ለመፍታት በተደረገው ጥረትም በጥቁር ገበያ ዱቄቱን አየር በአየርና ግራም ቀንሰው ዳቦ ሲሸጡ የተደረሰባቸው  660 ነጋዴዎች ላይ ትስስሩን የማቋረጥና የማስጠንቀቂያ እርምጃ መወሰዱን  አስታውቀዋል።

የተካሄደውን የዳሰሳ ጥናት መሰረት ያደረገ ሰነድ በቀጣይ ቢሮው አዘጋጅቶ ለክልሉ ካቢኔ በማቅረብ  በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ዳቦ አምራቾች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ደጀኔ  እንዳሉት የዳሰሳ ጥናቱ የተካሄደው በክልሉ ሰባት ከተሞች በሚገኙ 216 ዳቦ ቤቶች ላይ ነው።

ትስስር የሚፈጠርላቸው የዳቦ ቤቶች ማቅረብ የሚገባቸው 150 ግራም ዳቦ መሆኑን ጠቁመው፤ እየቀረበ ያለው ግን ከ75 እስከ 120 ግራም መሆኑን በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል።

 አቶ ተስፋዬ እንዳመለከቱት ጥናቱ ከተካሄደባቸው ዳቦ ቤቶች ውስጥም 95 በመቶ የሚሆኑት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በመሻት እስከ 50 በመቶ የዳቦውን መጠን በመቀነስ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ የሚያቀርቡ መሆናቸው ተደርሶበታል።

ችግሩ እንዲከሰት ያደረገውም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች የጥቅም ተጋሪ ሆነው መገኘት፣  የክትትልና ቁጥጥር ስራው አናሳ መሆንና ህብረተሰቡም መብቱን ማስከበር አለመቻሉ መሆናቸው ተጠቅሷል።

በጥናቱ ግኝት መሰረትም ከፍተኛ ዳቦ የማምረት አቅም ላላቸው ውሱን ዳቦ ቤቶችን መርጦ መስጠት፣ ዱቄቱ በቀጥታ ለማህበረሰቡ  ማቅረብ የሚሉ መፍትሄዎች ተመላክተዋል።

“የክትትልና ቁጥጥሩ መላላት በመንግስት ድጎማ የሚቀርበው ስንዴ ለታሰበው ዓላማ እንዳይውል አድርጎታል” ያሉት ደግሞ የግል ኢንዱስትሪዎች አማካሪ አቶ ብርቁ መለሰ ናቸው።

በዚህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት በዘላቂነት የሚያረጋግጥ ትክክለኛ የአሰራርና ስርዓት በመዘርጋት ችግሩን መፍታት  ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

በዳሰሳ ጥናቱ ግኝት ውይይት የንግድና ዘርፍ ማህበራት፣ የዳቦ አምራቾች ማህበር፣ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በአማራ ክልል ሶስት ሺህ 500 ዳቦ ቤቶች እንደሚገኙ ከንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።