የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ ለችግር ለተጋለጡ 600 ሰዎች ድጋፍ አደረገ

1373

ሰቆጣ፣ ሰኔ 22/2012 (ኢዜአ) የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ በኮረና ቫይረስ መከሰት ምክንያት በዋግሕምራ ብሄረሰብ ለችግር ለተጋለጡ 600 ሰዎች ድጋፍ አደረገ፡፡

በድጋፍ ርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የመማክርቱ አባልና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ዳዊት መኮንን እንደገለጹት  የዋግ ህዝብ በችግርም ውስጥ ሆኖ በህዝባዊ ወገኝተኝነቱና በአላማ ፅናቱ የማያወላውል ነው፡፡

ለኢትዮጵያ አንድነት መስዕዋትነት የከፈለው የዋግ ህዝብ በዚህ ወቅታዊ ችግር ለማህበራዊ ቀውስ እንዳይጋለጥ መማክርት ጉባዔው  የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

ድጋፉም ከመማክርት ጉባዔ አባላቱ በተሰበሰበ ገንዘብ በጊዜያዊነት 150 ኩንታል የምግብ ዱቄት አስረክቧል።

በቀጣይም ባለሃብቶችን ፤ ድርጅቶችን እና ሌሎች የአካባቢው ተቆርቋሪዎችን በማስተባበር ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የዋግ ህዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በዘላቂነት እንዲፈቱም በጥናት እና ምርምር የታገዙ ሌሎች ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ እና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስ ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊ ተፅእኖ ለማቃለል ቀደም ሲል 400 ሺህ ብር ግምት ያላቸውን የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በዛሬው እለትም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይም እንደ ችግሩ የስፋት መጠን ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋየ ገብሬ እንደገለፁት እስከ አሁን በተካሔደው የሀብት ማሰባሰብ ስራ 13 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተገኝቷል።

የሙሁራን መማክርት ጉባዔው የአካባቢውን ወቅታዊ ችግር በመረዳት ላደረገው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም  የተደራጁ ድጋፎች እንዲደረጉ ጠይቀዋል፡፡

ድጋፍ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል የአካል ጉዳተኛው ወጣት ምህረትአብ ዘውዱ እንዳለው ድጋፉ ወቅቱን የጠበቀ እና ላጋጠመው ችግር መፍትሔ የሰጠ ነው ብሏል።

በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተንቀሳቅሶ ለመስራት ባለመቻሉ ምክንያት የእለት ምግቡን ለመሸፈን ተቸግሮ እንደነበር የተናገረው ወጣት ምህረትአብ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በድጋፍ ስነስርዓቱ ላይ የመማክርት ጉባዔው አባላት ፤ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።