በትራንስፖርትና በገበያ ሥፍራዎች ኮሮናቫይረስን በመከላከል ረገድ ክፍተቶች እየተስተዋሉ ነው

1467

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22/2012 (ኢዜአ) በትራንስፖርትና በገበያ ሥፍራዎች የኮሮናቫይረስን በመከላከል ረገድ ክፍተቶች እየተስተዋሉ መሆኑን የሚኒስትሮች ኮሚቴ ገለጸ።

ወረርሽኙን ለመከላከል በድንበር አካባቢ ስድስት ኬላዎች ተከፍተው ወደ ሥራ መግባታቸውም ተገልጿል።

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ዛሬ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

የሰላም ሚኒስትርና የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የተከናወነውን ግምገማ በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ማኅበረሰቡ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ሥልቶች ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ መሻሻል ማሳየቱን ኮሚቴው በአዎንታዊ ጎኑ መገምገሙን ገልጸዋል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎቹ ከዚህ የበለጠ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡንም ገልጸዋል።

የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችንና የግል ንጽሕናን ከመጠበቅ አኳያም የታየው መሻሻል የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ይሁንና በትራንስፖርትና በገበያ ሥፍራዎች አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅና የመከላከያ እርምጃዎችን በተሟላ መልኩ ከመጠቀም አኳያ ክፍተቶች መኖራቸው ኮሚቴው ገምግሟል ብለዋል።

የምርመራ አቅሙ ባደገ ቁጥር በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ አይቀሬ በመሆኑ በተለይ ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ነገሮችን በቅንጅት መመከት ያስፈልጋል ብለዋል።

ተጋላጭነትን ለመቀነስ ኮሚቴው ያስቀመጠው አቅጣጫ መኖሩንና ይህ አቅጣጫ የእያንዳንዱን ዜጋ ውሳኔና ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በድንበር አካባቢ ስድስት ኬላዎች ተከፍተው ወደ ሥራ መግባታቸውንም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።

በድንበር አካባቢ ያሉ ኢ-መደበኛ መንገዶች ላይም ከአካባቢው የፀጥታ አካላትና ኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር እንዲጠበቁ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር ሂደት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ የጥንቃቄ እርምጃዎችን አስገዳጅ የሆኑት ከበሽታው መከላከል አንዱ በመሆኑ ነው ብለዋል።

የቫይረሱን መከላከያ ዘዴዎች ከመተግበር አኳያ ወጣ ያለ እርምጃ ሲወሰድም የሕግ ተጠያቂነት መኖሩን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጅና በየደረጃው ኮሚቴዎችን በማቋቋም የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።