ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ቻይና እንደምትደግፍ አረጋገጠች

56

ሰኔ 22/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ዛሬ ከቻይና ስቴት ካውንስልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሆኑት ዋንግ ዪ ጋር የስልክ ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም በሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ሁለቱ አገራት ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት አስታውቋል።

አቶ ገዱ የቻይና መንግሥት ''በቤልት እና ሮድ ኢንሼቲቭ'' አማካኝነት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት የሚያስችል የቻይና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤን በተሳካ ሁኔታ በመካሄዱ ደስታቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም በቅርቡ የሚኒስትሮች ቨርችዋል ኮንፍረንስን በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ በመቻላቸውም የተሰማቸውን ደስታ መግለጻቸውን ቃልአቀባዩ አስታውቋል።

በተጨማሪም የኮቪድ ወረርሽኝን ለመግታት ቻይና ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው ድጋፍ አቶ ገዱ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለመግታት ከቻይና ጋር የጀመረችውን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም አቶ ገዱ ገልጸዋል።

በተመሣሣይ አቶ ገዱ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ሴሪል ራማፎሳ ሰብሳቢነት የተካሄደውን አስቸኳይ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ቢሮ ቨርችዋል ስብሰባና ውሳኔ ገለጻ አድርገዋል።

መሪዎቹ የናይልና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ ከአፍሪካ የሚመነጭ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው መስማማታቸውን አቶ ገዱ ተናግረዋል።

በዚሁ መሠረትም በግድቡ ሙሊትና አስተዳደር ላይ የሚደረገው ድርድር በሚቀጥሉት ሁለት ሣምንታት እንደሚጠናቀቅ መስማማታቸውን አቶ ገዱ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩን መመልከት መጀመሩን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲገልጥ መወሰኑን አቶ ገዱ ማብራራታቸውን ቃልአቀባዩ አመልክቷል።

በመሆኑም ጉዳዩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል መታየት በጀመረበት አግባብ እንዲፈታ ቻይና ድጋፏን እንድታደርግ አቶ ገዱ በነበራቸው የስልክ ውይይት መጠየቃቸውንም አስታውቋል።

ዋንግ ዪ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵየ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጸዋል።ቻይና ያላትን ትብብርም ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል ዋንግ ዪ መግለጻቸውን ቃልአቀባዩ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ዋንግ ዪ በነበራቸው ውይይት ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም