የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ የጸረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ይቀጥላል ተባለ

1680

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22/2012(ኢዜአ) በመዲናዋ በሚገኙ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ የሚደረገው የጸረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በዛሬው እለት በጤና ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ውስጥ የጸረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት አካሄዷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ሁንድማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በግለሰብ ደረጃ ብቻ በሚደረግ የጥንቃቄ ተግባር የኮሮናቫይረስን የመከላከሉን ተግባር የተሟላ ለውጥ አያመጣም።

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ መሆኑን አመላክተው፤ ይህን የሚመጥን የጥንቃቄ እርምጃ መከተል ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ ይህን በመገንዘብ በመዲናዋ በሚገኙ ህዝብ በሚበዛባቸው በርካታ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ የጸረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት አካሄዷል ነው ያሉት።

የግል ንግድ ተቋማትም መሰል እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ባለስልጣኑ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት የጀመረውን የጸረ ኬሚካል ርጭት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የርጭት ስራው ከባለስልጣኑ እውቅና ሰርተፍኬት ባላቸው ተቋማት ብቻ መካሄድ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

እውቅና በሌላቸው ድርጅቶች የሚደረግ ርጭት ካለ ለከፋ የጤና ችግር እነደሚያጋልጥ አብራርተዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እውቅና ሳይኖራቸው ርጭት የሚያካሄዱ ድርጅቶች እንዳሉ ጥቆማዎች እየደረሳቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አንጻር ተገቢውን ጥንቃቄ መድረግ እንዳለበት መክረዋል።

የእውቅና ሰርተፍኬት ሳይኖራቸው ርጭት በሚያደርጉ ድርጅቶች ላይም አስፈላጊው ክትትል ተደርጎ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።